ከዓለት የጠነከረው የትዕግስት “ትዕግስት” እና “ጽናት”

AMN – መስከረም 17/2019 ዓ.ም

በበርሊን ዓመታዊው የማራቶን ውድድር የሴቶች የማራቶን ውድድር የአሸናፊዋ የትዕግስት አሰፋ የመጨረሻዎቹ ሁለት ኪሎ ሜትር ሲቀራት ያሳየችው ከዓለት የጠነከረ ጽናት ለትውልድ የሚተርፍ አርአያነት ያለው ተግባር ነው።

ትዕግሥት ሀገር ናት፣ ሀገራችን ዛሬም ልጅ አላት ብለን እንድናስብ ያደረገች ብቻ ሳይሆን ትዕግስት ሌላኛው የኢትዮጵያዊነት ትምህርት ናት።

የትዕግስት የዓላማ ጽናት ምስጢር የገንዘብ፣ የብርና የሀብት ጉዳይ አይደለም ለዚህ ደግሞ ትልቁ ማሳያ ትዕግስት ባለፈው ዓመት በመድረኩ ብዙ ገንዘብ፣ ዝናና ክብር አግኝታለች፤ መሻቷ ብር ያለመሆኑን ከዚህ በላይ ማሳያ የለም። ጉዳዩ የሰንደቅ ዓላማ፣ የሀገር የክብርና የማንነት እንጂ።

ምክንያቱም ትዕግስት የአበበ ቢቂላ፣ የሀይሌ፣ የደራርቱ ፣ የቀነኒሳ እንዲሁም የብዙ ጀግኖች ሀገር ልጅ ናት። አሷን የሚያስጨንቃት አሸንፋ የምታገኘው ብርና ወርቅ አይደለም ይልቁንም እያመማት እና እያነከሰች የጨረሰችው ሁለት ሺህ ሜትር የሀገር አደራና የሰንደቅ ዓላማ ፍቅር ነው።

ይህ ባይሆንማ ኖሮ ህመሟን ለማስታገስ እና በቶሎ ለማገገም ውድድሩን ማቋረጥ ትችል ነበር፡፡ ምክንያቱም በህመም ሳቢያ ውድድርን ሳይጨርሱ ማቋረጥ የተለመደና ነውና፤ ይሁንና ትዕግስት ይህንን አላደረገችም።

ህመሟን ታግሳ የጀመረችውን መጨረስ እንዳለባት እና ጉዳዩ የሀገር፣ የሰንደቅ ዓላማ እና ያልበገር ባይነት የጥንት ኢትዮጵያውያን የሁልጊዜ ተግባር ማሳያ ሌላኛው ምልክት መሆኑን ስላመነችበት ነው።

ስምን መልዐክ ያወጣዋል እንዲሉ የትዕግስት “ትዕግስት” የብዙ ነገሮች ማሳያ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ነው። ትናንት በአድዋ የውጭ ወረራ የመከትንበት፣ አበበ ቢቂላ በባዱ እግሩ ቶኪዮ ላይ ሀገሩን ያስጠራበት፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብን አትጀምሩም ከጀመራችሁም አትጨርሱም የተባልነውን ጨርሰን ያሳየንበት ድርብ ድርብርብ ድል አመላካች እና ልዩ ማሳያ ሆኖ ያገለግላል።

ትዕግስት እያነከሰች የጨረሰችው ማራቶንን ብቻ አይደለም የአልሸነፍም ባይነት፣ የእውነተኛ እና የታላቅነት መገለጫ የሆነው የዓላማ ጽናት እና ቁርጠኛነት እና የታላቅነት መገለጫን ምልክት እንጂ።

የእሷ እያነከሱ የመጨረስ ሌላኛው ትርጉም ፈተናና መከራ ቢኖርም ጽናት ካለ የማይቻል ነገር እንደሌለ የሚያስተምር ነው። ይህን መሠሉን ተግባር ደግሞ በኢትዮጵያውያን ሲከወን ለዓለም ልዩ ትርጉም አለው፡፡

የሆነው ሆኖ ወላጆቿ ሥም ሲያወጡላት ትዕግስት ብለው የመሰየማቸው ምስጢር በዕርግጥም ስምን መልዐክ ያወጣዋል ያስብላልና እኛስ ከትዕግስት “ትዕግስት” ምን እንማር ምንስ እንወቅ ?

በታሪኩ ለገሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review