የትግራይ ህዝብ ሕገ-ወጡ ሕወሃትን ከጫንቃው በማውረድ ሰላምና ልማትን ማፋጠን አለበት

AMN- ነሐሴ 12/2018 ዓ.ም

የትግራይ ህዝብ ሕገ-ወጡ ሕወሃትን ከጫንቃው በማውረድ ሰላምና ልማትን ማፋጠን እንዳለበት የቀድሞው ወታደራዊ አመራር ሌተናል ጀኔራል ዮሐንስ ገብረ መስቀል ተናገሩ፡፡

ሌተናል ጄኔራል ዮሐንስ ገብረመስቀል ፤ ‘ጽምዶ” በሚል ስያሜ የተሰባሰቡ ኃይሎች በሥልጣን ጥማት የሰከሩና እርስ በእርሳቸው የማይተማመኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ጥምረቱም የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች የሀገርን ዕድገትና ብልጽግና ጉዞ የማዳከም ዓላማ በማንገብ የሚንቀሳቀሱ ፀረ-ሕዝብ ኃይሎች የወጠኑት መሆኑን ተናግረዋል።

የሻዕቢያ ኃይል ከጥፋት ውጪ የልማትና ዕድገት ትብብር አይታየውም ያሉት ሌተናል ጄኔራል ዮሐንስ፤ ኤርትራንም የልማት ሽታ የማያውቃት የስደት፣ ሞትና እንግልት ምድር አድርጓት መቀጠሉን ገልጸዋል።

የሕገ-ወጡ ሕወሃትን፣ የኦሮሚያና አማራ ክልል ጽንፈኛ ኃይሎችን ”ጽምዶ” በሚል ስያሜ ያለ አንዳች ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለጥፋት ዓላማው ማስፈጸሚያነት በማጣመር ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

የ”ጽምዶ” ጥምረትም ተስፋ መቁረጥ የወለደው ያለአቻ ጋብቻ የጥፋት እንቅስቃሴ መሆኑን አብራርተዋል።

የ”ጽምዶ” ጥምረትም በሻዕቢያ የበላይ ጠባቂ ኢሳያስ አፈወርቂ ቀጭን ትዕዛዝ የሚመራና በራሱ የመወሰን አቅም የሌለው፣ የኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ታሪካዊ ጠላቶች ዓላማ አስፈጻሚ ነው ብለዋል።

የጥፋት ጥምረቱ በታሪካዊ ጠላቶች በሚሰፈርለት ቀለብ ልክ የሚያሰራጨው ስሁት ፕሮፓጋንዳም ሕዝብን በማወናበድ ላይ የተመሠረተ መሠረተ ቢስ ስብስብ መሆኑን በተግባር እንደሚያመላክት ገልጸዋል።

ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን በጥፋት ጥምረቱ የ”ጽምዶ” ስብስብ የፈጠረው ያልተቀደሰ ጋብቻም ከጥፋት አጋሩ ሻዕቢያ የቀሰመው የአጥፍቶ ጠፊነት ባህሪ መሆኑን አንስተዋል።

የትግራይ ሕዝብ ጠላት በክልሉ በቅሎ ከጎለመሰው ሕገ-ወጡ የሕወሓት ስብስብ በተጨማሪ ሻዕቢያ ቁጥር አንድ መሆኑም አስገንዝበዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review