AMN – መስከረም 24/2019
ኢትዮጵያ ከ7ኛ ጠቅላላ ምርጫ በኋላ መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም የኢፌዴሪ መንግስት ምስረታና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉባዔ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ታካሂዳለች፡፡
7ኛዉ ጠቅላላ ምርጫ ለኢትዮጵያዊያን የምርጫ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በርካታ ዕድሎች እና ፈተናዎች የታዩበት ወቅት ነበር፡፡
ምርጫዉ በሀገሪቱ ታሪክ ከፍተኛ ቁጥር ያለው መራጭ የተመዘገበበትና ድምጽ የሰጠበት፤ ዴሞክራሲያዊ፤ አሳታፊና ግልጽ እንደነበር የሀገር ውስጥ እና የውጭ ታዛቢዎች ጭምር መስክረዋል፡፡
በርካታ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫ የተወዳደሩበት፤ በነጻነት ሃሳባቸውን የሸጡበት እና በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ልምምድ ውስጥ የድርሻቸውን ያበረከቱበት ነበር፡፡
በድምጽ መስጫ ዕለትም ቢሆን መራጩ ህዝብ የሌሊት ብርዱ፤ የቀን ሃሩሩ፤ ረሃብና ድካሙ ሳይበግረው በጽናት ቆሞ ድምጹን የሰጠበት ምርጫ ነበር፡፡
ምርጫው በህዝብ የተመረጠን መንግስት ለመሰየም የተደረገ ብቻም ሳይሆን የሀገር ሉዓላዊነትን ያረጋገጠም ነበር፡፡
የኢትዮጵያን ምርጫ ማካሄድና መንግስት መመስረት ቀርቶ የሀገሪቱን በሰላም ውሎ ማደር የማይሹ እንደ ህገወጡ የህወሃት ቡድን፤ ሻዕቢያ እና ጽምዶ ያሉ ጽንፈኛ ኃይሎች በግልጽም ሆነ በስውር ምርጫውን ለማደናቀፍ በርካታ ጥፋቶችን ሲፈጽሙ ቆይተዋል፡፡
መራጮች እንዳይመዘገቡ፤ የምርጫ ቁሳቁሶች እንዳይጓጓዙና መራጮች ወጥተው ድምጽ እንዳይሰጡ የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል፡፡
የህወሃት ቡድንና የሻዕቢያ ዋንኛ ተልእኮ ሀገሪቱን መንግስት አልባ ማድረግ እንደሆነ የተረዱት ኢትዮጵያንም በጽንፈኛ ሃይሎቹ ዛቻና ማስፈራሪ ሳይሸበሩ በነቂስ ወጥተው ድምጽ በመስጠት ጠላቶቻቸውን አሳፍረዋል፡፡
በምርጫው የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የህዝቡን ድምጽ አክብረው የተቀበሉ ሲሆን ምርጫው ዴሞክራሲያዊ እንደነበርም መስክረዋል፡፡
በተካሄደው ህዝባዊ ምርጫ መሰረት ብልጽግና ፓርቲ አብላጫውን ድምጽ አግኝቶ ያሸነፈ ሲሆን አሁን ላይ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮችን የመንግስት ምስረታ ሂደቱን በስኬት አጠናቋል፡፡
የኢፌዴሪ የመንግስት ምስረታና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመክፈቻ ጉባኤ መስከረም 25 ቀን 2019 የሚካሄድ ሲሆን በዚህ ጉባዔ ላይም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ያሸነፉ የህዝብ ተመራጮች ይሳተፉበታል፡፡
የታሪካዊ ጠላቶቿ በውስጥና በውጭ የከፈቱባትን ትንኮሳዎችንና ፈተናዎችን በህዝቦቿ ቁርጠኝነትና ጽናት ያሸነፈችው ኢትዮጵያ በሀገሪቱ የመንግስት ምስረታ ሂደት አዲስ ታሪክ ትሰራለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ህገወጡ ህወሃትና ሻዕቢያ የሀገሪቱን የመንግስት ምስረታ ሂደት ለማደናቀፍ ሰሞኑን ጽምዶ የሚባል ጥምረት ፈጠረው በሀገሪቱ ላይ ጦርነት ቢከፍቱም በለኮሱት እሳት በመቃጠል ላይ ይገኛሉ፡፡
ኢትዮጵያ ታሪካዊውን የመንግስት ምስረታ የምታካሄደው ህገወጥ ቡድኑ ከትግራይ ክልል እየጸዳ ባለበትና በክልሉ ህዝባዊ ምርጫ ለማካሄድ በታቀደበት ወቅት መሆኑ ደግሞ ልዩ ያደርገዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ