የኦሮሞ ህዝብ በትግሉ ነፃ ወጥቷል!

You are currently viewing የኦሮሞ ህዝብ በትግሉ ነፃ ወጥቷል!

AMN መስከረም 24/2019

የኦሮሞ ህዝብ ላለፉት ረጅም አመታት ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ጨምሮ ቋንቋዉ፤ ባህሉ እና እሴቶች እንዲከበርለት አጥብቆ ሲጠይቅ ቆይቷል፡፡

የኦሮሞ ህዝብ ይህንን ጥያቄ ለመጠየቅ የተገደደዉ ባለፉት መንግስታዊ ሥርዓቶች ዉስጥ ራሱን በራሱ ማስተዳደር ባለመቻሉ፤ በቋንቋዉ ለመማር እና ለመተዳደር ፤ እንደ ገዳ ሥርዓትና ኢሬቻ ያሉ ባህሎቹንና ታሪኮቹን ማሳደግ እና ማጠናከር ባለመቻሉ ነበር፡፡

አንዳንድ የኦሮሞ ምሁራን እንደሚገልጹት ከሆነ የኦሮሞ ህዝብ በሃገረ መንግስት ግንባታ እና የሃገሪቱን ሉዓላዊነትና ህልዉና በማስከበር ሂደት ዉስጥ የአንበሳዉን ድርሻ ቢኖረዉም በቋንቋዉ የመናገር፤ የመማር፤ የመተዳደር፤ ባህልና እሴቶቹን የመጠቀም፤ የማሳደግና የማጠናከር መብት አላገኘም፡፡

የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለዉ መሆኑን የሚገልጹት ምሁራኑ ዴሞክራሲያዊ እና ህገመንግስታዊ መብቶቹ እንዲከበሩለት ከመጠየቅ ዉጪ ማንንም የመጫን፤ የመግፋትና የመጉዳት አለማ የለዉም፡፡

የኦሮሞ ህዝብ ሌላዉን አቅፎ በጋራ የሚኖር፤ ፍትህ እና ሰፉ የሚያከብር፤ ለሰዉ ልጆች ብቻ ሳይሆን ለፍጥረታት እንኳ ትልቅ ክብር ያለዉ፤ የተቸገረን የሚረዳና ያለዉን አካፍሎ የሚኖር፤ እዉነት ወይም ሃቅ ከተዛነፈ የሰለጠነ የፍርድ ስርዓት ያለዉ ህዝብ ነዉ ይላሉ፡፡

የኦሮሞ ህዝብ የዘመናዊዉ ዴሞክራሲ መገለጫ በሆነዉ እና አለም በመሰከረለት በገዳ ሥርዓት የሚተዳደር ስልጡን ህዝብ ነዉ፡፡

የለዉጡ መንግስት ወደ አመራርነት ከመጣበት ጊዜ አንስቶ የኦሮሞ ህዝብ ያነሳቸዉን ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የመብት ጥያቄዎችን በሂደት ለመመለስ በርካታ የለዉጥ እርምጃዎችን በመዉሰድ ላይ ይገኛል፡፡

በባህል ልማት ረገድ በተወሰደዉ እርምጃ የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ ወደ መልካው ተመልሶ ስርዓት ውስጥ እንዲገባ የተደረገ ሲሆን የሆራ ሀርሰዴ ኢሬቻ ደግሞ በቢሾፍቱ ውበት ደምቆ ከፍ ብሎ እንዲከበር ተደርጓል፡፡

ዛሬ ላይ የኦሮሞ ህዝብ ከመቸዉም ጊዜ በላይ በለዉጡ መንግስት ባገኘዉ መብት ተጠቅሞ፤ ከሃገር ዉስጥ እና ከዉጭ ሃገራት ጭምር በሆረ ፊንፊኔ እና ሆረ ሃርሰዴ የኢሬቻ በዓላት ላይ ተሰባስቦ፤ በባህላዊ አልባሳት ደምቆ፤ ሆ ያ መሬዎ እያለ ወደ መልካ ወርዶ ፤ ፈጣሪዉን አመስግኖ፤ ተመራርቆና ተጠያይቆ የአመት ሰዉ ይበለን ብሎ ይለያያል፡፡

የበዓሉ ታዳሚዎች በኢሬቻ በዓል አከባበር ላይ የሚያሳዩት አንድነትና ህብረት፤ ለገዳ ሥርዓት ያላቸዉ ታዛዥነት፤ ኢሬቻን በነጻነት በማክበራቸዉ የሚሰማቸዉ ደስታ፤ የባህላዊ አልባሳት ድምቀት፤ የባህላዊ ምግቦችና መጠጦች መስተንግዶ እና ሌሎች የበዓሉ ኩነቶች የሃገር ገጽታን እና ኢኮኖሚዉን ከመገንባት አልፈዉ በርካታ ቱሪስቶች በበአሉ ላይ እንዲታደሙ ትልቅ እድል ፈጥሯል፡፡

በተለይ ኢሬቻ ለኦሮሞ ህዝብ የክረምት ወቅት አልፎ ብራ በመድረሱ ፈጣሪዉን የሚያመሰግንበት ሥርዓት ብቻ ሳይሆን አንድነቱንና ህብረቱን የሚያጠናክርበት ትልቅ መድረክም ጭምር ነዉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የዘንድሮዉን የኢሬቻ በዓል አስመልክቶ ባስተላለፉት መልእክት ህዝባችን በትግሉ ያመጣዉ ለውጥ ከብራ ጋር ይመሳሰላል ይላሉ፡፡

የኦሮሞ ህዝብ ቋንቋውን፣ ባህሉንና እሴቱን ለማሳደግ ያነሣውን ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ለመመለስ በተሰራዉ ስራ በባህል ልማት ረገድ የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ ወደ መልካው ተመልሶ ስርዓት ውስጥ መግባቱ፤ የሆራ ሀርሰዴ ኢሬቻ ደግሞ በቢሾፍቱ ውብት ደምቆ ከፍ ብሎ መከበሩ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የገዳ ስርዓት እሴትን መነሻ በማድረግ የሀሳብ ልዩነትን በመደማመጥ ለማስተካከል ሀገራዊ ውይይት መደረጉንም ነዉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡

አሁን የምንገነባው ስልጣኔ በጥንታዊ እሴቶቻችን ላይ የተመሠረተ እና በመደመር ፍልስፍና የታቀደ ነዉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለጋራ እውቀት፣ የገዳና የሰፉ ትምህርት፣ ለጋራ ፍትህ ባህላዊ ሸንጎዎችን አቋቁመን፣ ለጋራ ልማት የዜግነት አገልግሎትን ዘርግተን፣ ለጋራ ደህንነት ደግሞ የስርዓቱን ጠባቂዎች አደራጅተን ስርዓት እየገነባን እንገኛለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ፈተናዎች ግን አሁንም ይኖራሉ፤ ለኢትዮጵያ መውጣት የጀመረው ይህ የለውጥ ብርሃን ግን በየትኛውም የክረምት ጨለማ፣ ዶፍና ጭቃ ተንሸራትቶ ሊደናቀፍ አይችልም።

ምክንያቱም እነዚህ ፈተናዎች ከኢትዮጵያና ህዝቦቿ አቅም በታች ናቸው እንጂ ከህዝቡ በላይ አይደሉምና፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን አንድነቱን አጠናክሮ፣ ወንድማማችነትን አስፋፍቶ በፍቅር በመደመር የኢትዮጵያን ስልጣኔ እውን ለማድረግ እየተባበረ ይገኛል ሲሉ ነዉ የገለጹት፡፡

ኦሮሞ በትግሉ ነፃ ወጥቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በኋላ በጠብመንጃ አፈሙዝና ከጠላት ጋራ በመወገን የሚመለስ የኦሮሞ ጥያቄ ፈፅሞ ሊኖር አይችልም ብለዋል፡፡

የሃገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም ወደ ጎን ትተዉ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጎን ለተሰለፉ ሃይሎች ባስተላለፉት መልእክት ኦሮሞ ‘ከሚያመሹበት የሚያድሩበት ቤት ይሻላል’ ብሎ እንደሚተርት ሁሉ አሁንም ፊታችሁን ወደ ሰላም መልሱ፤ የሰላም በር አሁንም እንደተከፈተ ያለ መሆኑን ላረጋግጥላቸው እወዳለሁ ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review