AMN- ነሐሴ 13/2018 ዓ.ም
ሙስና ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ቀውሶችን የሚያስከትል የሀገርን ዕድገት የሚፈታተን አደገኛ ድርጊት ነው፡፡
ሙስና እና ብልሹ አሰራር የህዝብን ሀብት ለግል ጥቅም በማዋል በሀገር እና በህዝብ ላይ የሚያደርሰው ጉዳትም ዘርፈ ብዙ ነው፡፡
ጉቦ መስጠት እና መቀበል፣ የህዝብ ሀብትን ማባከን እንዲሁም ህጋዊ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ሲባል የሐሰት ማስረጃዎችን ማዘጋጀት ወይም መረጃዎችን ማዛባት የሙስና እና ብልሹ አሰራር መገለጫ ናቸው፡፡
የህግ የበላይነትን አለማክበር፣ የሀገር ፍቅር እየተሸረሸረ መምጣት እና የሥነ-ምግባር ግድፈት ለሙስና መስፋፋት ዋና ዋና ምክንያቶች እንደሆኑ ይጠቀሳል፡፡
ሙስና የሰላም፣ የዴሞክራሲ እና የኢኮኖሚ ዕድገት ዋናው እንቅፋት ሲሆን ሀብትን ከብዙዎች ወደጥቂት ግለሰቦች እንዲዛወር በማድረግ ድህነትን ያባብሳል። ከዚህ ባለፈም ለሀገር ልማት መዋል የሚገባው ገንዘብ በግለሰቦች ኪስ ሲገባ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ይቀንሳል፡፡
በተቋማት የሚገለገለው ህዝብ ጥራት የሌለው አገልግሎት እንዲያገኝና ለከፍተኛ እንግልት እንዲዳረግም ያደርጋል፡፡ በዚህም መንግስት በቅርቡ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ሌብነት እና ህገ-ወጥነት ላይ በጥናት የተመሰረተ ርምጃ ወስዷል፡፡
ይህም የህዝብ ጥቅም የሚያስከብር፣ የህግ የበላይነትን የሚያረጋግጥ፣ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትንና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን ነው፡፡
ሙስናን እና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ሲሆን መንግሥትና የፍትሕ አካላት የጀመሩት የጸረ ሙስና ትግል እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
በኢትዮጵያ የሚስተዋለውን የሙስና እና ብልሹ አሠራር ተጋላጭነት ለመከላከል የትውልድ ሥነ-ምግባር ግንባታ ላይ በትኩረት መሥራት አስፈላጊ እንደሆነ ይታመናል፡፡
ይህም ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ድረስ ሐቀኝነትን፣ ታታሪነትን እና ትጉህ ትውልድን ለመገንባት ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡
ወንጀለኞችን በህግ ፊት መቅጣት እና ጠንካራ የፀረ-ሙስና ተቋማትን ማጠናከርም ይገባል።
የሻምበል ምህረት