AMN- ነሐሴ 18/2018 ዓ.ም
ከተማ አስተዳደሩ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች የሚገለጡበት የአዲስ አበባ ከተማ የባህል ማዕከል ለመገንባት እየሰራ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ኪነ-ጥበብ ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
የቢሮ ኃላፊዋ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) ለኤ ኤም ኤን እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የበዓላት ቀናት በአብዛኛው ነሐሴ ወር ላይ የሚጀምሩ መሆናቸውን አንስተው፣ በበጀት ዓመቱ የከተማዋን ነዋሪ እርስ በእርስ በባህል የሚያስተሳስር ስራ መሰራቱን አስታውሰዋል፡፡
የሚከበሩ በዓላትም እሴታቸውን ጠብቀው ለትውልድ መተላለፍ አለባቸው በሚል መርህ ለአብሮነት፣ ለእድገት፣ ለትስስር፣ ለሰላም እንዲሁም ለልማት ጠቃሚ የሆኑ እሴቶችን ለመለየት የሚያስችሉ መድረኮች እየተካሄዱ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ከተማዋ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በዓላት የሚከበርባትና የሚገለጥባት ከተማ መሆኗን በመግለጽ ነዋሪውም የበዓላቱን እሴት ተገንዝቦ አንዱ የሌላውን ባህል የሚያከብርባት ከተማ ሆናለችም ብለዋል፡፡

ይህም አዲስ አበበ የኢትዮጵያ ትልቋ የባህል ሞዛይክ የሚታይባት ከተማ እንድትሆን ከተማ አስተዳደሩ የሰራው ስራ ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሃገር በቀል እውቀት ላይ ከባህላዊ አልባሳት ጀምሮ እስከ ባህላዊ ህክምና ድረስ ያለው ትስስር እየተዋወቀ እና እየተጠና ነው ያሉት ሂሩት ካሳው (ዶ/ር)፤ ለዚህም አዲስ አበባ የኪነ ጥበብ ማዕከል ሆናለች ብለዋል፡፡
በከተማዋ በአንድ ዓመት ብቻ 1ሺህ 333 የኪነ ጥበብ መድረኮች እንደተዘጋጁ ጠቅሰው አርቲስቶች በስራዎቻቸው ላይ እርስ በእርስ እንዲነጋገሩ እና እንዲተራረሙ የሂስ መድረክም ሳይቆረጥ እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በአዲስ አበባ 242 የሚሆኑ “የአርት” ኢንተርፕራይዞች እንዳሉ የገለጹት የቢሮ ሀላፊዋ ለእነዚህም ድጋፍ፣ ክትትልና ቁጥጥር ይደረግላቸዋል ብለዋል፡፡
እንዲሁም ከተማዋ ብዙ ቅርሶች የተመዘገቡባት እንደመሆኗ መጠን አስተዳደሩ በርካታ ቅርሶችን ጠግኗል ያሉት ሂሩት ካሳው ()ዶ/ር)፤ ቅርስ ጥገና በራሱ ዲዛይን የሚሰራ በመሆኑ ከፍተኛ በጀት እና የጥገና እውቀት እንደሚጠይቅም ጠቁመዋል፡፡
በየሻምበል ምህረት