AMN- ነሐሴ 18/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ልዩነቶችን በውይይትና በሰለጠነ መንገድ የመፍታት፣ አብሮነትን የማጠናከር እና ለነገዋ ሀገር አስተማማኝ መሰረት የመጣል ታሪካዊ ሂደቷን በስኬት በማካሄድ ላይ ትገኛለች።
በተለያዩ ክልሎችና የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ሲካሄድ የቆየው ሀገራዊ የምክክር ሂደት፣ ዜጎች በሀገራቸው የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ በነጻነት የመከሩበትና ቀናው መንገድ የተቀየሰበት አጋጣሚ ሆኗል።
ይህ የምክክር መድረክ ከተለያዩ የሀገሪቱ ማህበረሰብ ክፍሎች የወጡ በርካታ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ሲሆን፣ ሂደቱን በተመለከተ የተለያዩ ሀሳቦችና ምስክሮች ተሰጥተውበታል።
ተመካካሪዎቹ ፣ ለዘመናት በልባችን ተይዘው የቆዩ፣ ግጭትና ቅሬታ ሲፈጥሩ የነበሩ ሀሳቦችን በግልጽ ጠረጴዛ ዙሪያ አቅርበን ለመወያየት መቻላችን ትልቅ እፎይታ ነው፤ ይህ መድረክ አዲሷንና የበለጸገችዋን ኢትዮጵያ የመገንቢያ ትልቅ ዕድል ሰጥቶናል ሲሉ ተደምጠዋል።
የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ የህዝብን ድምፅ ማዳመጥ የቻለ፣ ሁሉንም አሳታፊ ያደረገ እና ለረጅም ጊዜ ዘላቂ ሰላም ማምጣት የሚያስችል መሰረት የጣለ እንደሆነም ገልጸዋል።
ምክክሩ የሀገሪቱን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት ብቸኛውና ትክክለኛው መንገድ ሰላማዊ ውይይት መሆኑንም አረጋግጧል።
ከተለያዩ አካላት የተሰበሰቡ ሀሳቦች በማቀናጀት፣ ለነገዋ ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋን የሚያበስር ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ምክክሩ አዲስ መንገድ ቀይሷል፡፡
ይህ ታሪካዊ የምክክር ሂደት የትናንት ቁስሎችን እያከመ፣ የዛሬውን አብሮነት እያጠናከረ እና የነገዋን ዘላቂ ሰላም የምታረጋግጥ ኢትዮጵያን ለመገንባት የተጣለ ትልቅ የታሪክ መሰረት ሆኗል።
በታምራት ቢሻው