AMN—ግንቦት 25/2018 ዓ.ም
በፖለቲካ ሳይንስና በሕዝባዊ አስተዳደር ትንታኔዎች መሠረት፣ ምርጫና ዴሞክራሲ የማይነጣጠሉ ጽንሰ-ሐሳቦች ናቸው።
ዴሞክራሲ የሕዝብ ሥልጣን ወይም በሕዝብ ለሕዝብ ከሕዝብ የሚመነጭ አስተዳደር ሲሆን፤ ምርጫ ደግሞ ይህ ሥልጣን በተግባር የሚገለጽበት፣ የሥልጣን ሕጋዊነት የሚረጋገጥበት እና ተጠያቂነት የሚሰፍንበት ዋናው መሣሪያ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡
በአጭሩ ዴሞክራሲ ግቡ ሲሆን፣ ምርጫ ደግሞ ያንን ግብ ለማሳካት የሚኬድበት ሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ እንደሆነ ነው የሚገለጸው፡፡
በዴሞክራሲ የበለጸጉ ሀገራት ምርጫን እንደ ብሔራዊ በዓል እና እንደ መደበኛ የፖሊሲ ውድድር አድርገው እንደሚቆጥሩት መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

በእነዚህ ሀገራት በምርጫው ከ80 በመቶው በላይ የሚሆን ከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ የሚታይበት ሲሆን፣ ውድድሩ በማንነት ላይ የሚያተኩር ሳይሆን በአማራጭ ሐሳብ ላይ የሚመሰረት ነው፡፡
ተፎካካሪዎች የፖለቲካ ፓርቲዎችም ውጤት በጸጋ የሚቀበሉ ሲሆን፣ በገለልተኛ ተቋማት ላይ ያላቸው እምነትም እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡
ታዲያ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርአት ባህል እንዲሆነ ለማድረግ የዴሞክራሲ ተቋማት ከመገንባትና ባሻገር የስምጣን ባለቤት ህዝብ አንዲሆንና በምርጫ ብቸ የማድረግ ልምምዶች እየዳበሩ መጥተዋል ለዚህም 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አንዱ ማሳየ ነው ፡፡
ኢትዮጵያም 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በትናንትናው እለት አካሂዳለች፡፡ በዚህ የምርጫ ሂደት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ወጥቶ ድምጽ መስጠት ችሏል፡፡

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች እስከ ሌሊቱ ስድስት ሰዓት (6:00) ድረስ በምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት ድምፅ የሰጡ ሲሆን፣ ይህም በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ባህልን ለመገንባትና ለማዳበር የተደረገ ትልቅ ታሪካዊ አስተዋፅኦ ተደርጎ የሚወሰድ ተግባር ነው፡፡
በምርጫው ዕለት ከፍተኛ ቁጥር ያለው መራጭ ህዝብ በጠዋት የወጣ ሲሆን፣ በአንዳንድ ምርጫ ጣቢያዎች በታየው ከፍተኛ መጨናነቅ ምክንያት የምርጫው ሰዓት እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ እንዲራዘም ተደርጓል።
ይህም ሆኖ የከተማዋ ነዋሪዎች ረጅም ሰዓታት የወሰደውን ሰልፍና የሌሊቱን ቅዝቃዜ ተቋቁመው፣ ድምፃቸውን ሰጥተዋል።
እንደ የፖለቲካና የዲሞክራሲ ተንታኞች፣ ህዝቡ እስከ ሌሊቱ 6፡00 ሰዓት ድረስ በትዕግስት ተሰልፎ መምረጡ ሶስት ዋና ዋና መልዕክቶችን ያስተላልፋል፡፡

የመጀመሪያው፣ ዜጎች ለራሳቸው የፖለቲካ ውሳኔና ለድምፃቸው የሰጡትን ከፍተኛ ዋጋና የንቃተ-ህሊናቸውን ከፍታ የሚያሳይ ሲሆን፤ ሁለተኛው፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አንድም መራጭ መብቱ እንዳይገደብ ለማድረግ የተከተለው አሰራር ይጠቀሳል፡፡
በሶስተኛ ደረጃ፣ ዜጎች በእኩለ ሌሊት ያለምንም ስጋት ወጥተው መምረጣቸው በከተማዋ የነበረውን አስተማማኝ የፀጥታና የደህንነት ሁኔታ ማሳያ ነው ፡፡
ይህ የነዋሪዎች ንቁ ተሳትፎና ያሳዩት የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል፣ በሀገሪቱ የሃሳብ ልዩነቶችን በምርጫ ካርድ የመፍታት ልምድን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረና ለዲሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ ትልቅ መሰረት የጣለ መሆኑም ተመልክቷል፡፡
በአስማረ መኮንን