AMN- ነሐሴ 18/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሀገር ውስጥ እና በመላው ዓለም ለሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለ1 ሺህ 501ኛው የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የልደት (መውሊድ) መታሰቢያ በዓል በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ በማለት የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፏል፡፡:
ጉባኤው ባስተላለፈው መልዕክት ፣ የዘንድሮው መውሊድ በዓል የሚከበረው ሀገራዊ ምክክሩ በስኬት በተጠናቀቀበት ማግስት መሆኑ የመታሰቢያ በዓሉን ደስታ እጥፍ ድርብ አድርጎታል ብሏል።
ለአንድ ወር ከ15 ቀናት ሲካሄድ የነበረው ሀገራዊ ምክክር ጠንካራ ክርክር፣ የሀሳብ እና የፍላጎት ልዩነት የታየበት ቢሆንም፣ በሂደት የሀገርን እና የሕዝብን ጥቅም በማስቀደም በመግባባት የተጠናቀቀ ታሪካዊ ስኬት መሆኑን ገልጿል።
ለዚህ ስኬትም የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች እና አገልጋዮች ያበረከቱት አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ እንደነበርና በቀጣይም ስምምነቶቹን በተግባር ከመተርጎም አንፃር ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ እምነቱ መሆኑን በመልዕክቱ ተመላክቷል።
እንደ ጉባኤው መግለጫ፣ የዚህ ዓመት መውሊድ “የፍትሑ ነብይ” በሚል መሪ ቃል የሚከበር ሲሆን፤ መሪ ቃሉ ነብዩ ሙሐመድ ለፍትህ የላቀ ትኩረት ሰጥተው እንደኖሩ እና እንዳገለገሉ ለማሰብ፣ ለማሰላሰል እና ለማውሳት እድል ይሰጣል።
የነብዩ መወለድ በምድር ላይ ሰፍኖ የነበረውን ኢሰብአዊነት፣ በደል፣ ሀጢአትና ርኩሰት ለማረም እና ለማስወገድ ከፍተኛ ሚና እንደነበረውና ሰብአዊ ክብርና ርህራሄ በምድር እንዲሰፍን መንገድ የጠረገ መሆኑን ገልጿል።
ነብዩ ሙሐመድ በኖሩበት ዘመን ሁሉ ለወገኖቻቸው ብቻ ሳይሆን ለሰው ዘር በሙሉ ሰብአዊነትን፣ ፍቅርን፣ አክብሮትን እና ርህራሄን ያሳዩ እንደነበርም በመልዕክቱ ተገልጿል።
የእምነቱ ተካታዮች በዓሉን ሲያከብሩ በተለመደው ኢትዮጵያዊ የመረዳዳት ባህል መሰረት በሕመም አልጋ ላይ፣ በሕግ ጥላ ስር እና በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በመጠየቅ፣ በማበረታታት እንዲሁም ያለንን በማካፈል ሊሆን እንደሚገባ ጥሪ ቀርቧል።
በዓሉ ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ለሕዝቦቿ አንድነት እና በረከት ከልብ የሆነ ዱዓ በማድረግ እንዲከበር መልዕክት የተላለፈ ሲሆን፣ ለኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አመራሮች እና ለመላው ተከታዮች የሰላም፣ የጤና እና የደስታ በዓል እንዲሆንላቸው የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተመኝቷል።