AMN – ነሐሴ 20/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያውያን ለበርካታ ዘመናት የሐሳብ ልዩነቶቻችንን በውይይት ከመፍታት ይልቅ የኃይል አማራጮችን ስንጠቀም ከርመናል። እነዚህ አማራጮች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በማባባስና ግጭቶችን በማፋፋም ከፍተኛ ሰብአዊ እና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እንዳስከተሉ የታሪክ መዛግብት እማኝ ናቸው።
የኃይል አማራጭ ያስከተለውን ዘመን ተሻጋሪ ኪሳራ የተረዳው የዚህ ዘመን ትውልድ በሀገራችን ኢትዮጵያ ዘመናትን የተሻገሩ ችግሮች መፍትሔ እንደሚያስፈልጋቸው በማመን የሀገራዊ ምክክር ሐሳብን ቀስ በቀስ በማጎልበት ወደ ተግባር ምዕራፍ አድርሶታል፡፡ ትውልዱ ከሐሳብም ወደ ተቋም አሸጋግሮታል፡፡
ከሐሳብ ወደ ተቋም
በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር እንዲካሄድ ፍላጎት የመጣው ከአንድ ወገን ብቻ አልነበረም። የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሀገሪቱ ውስጥ የሚስተዋሉትን ያለመግባባት አዙሪቶች በምክክር የሚፈቱበት መድረክ እንዲመቻች ለበርካታ ጊዜያት ሲወተውቱ ቆይተዋል።
ከዚህ ባሻገር እነዚህ አካላት በሌሎች ሀገራት ከተካሄዱ የሀገራዊ ምክክር ተሞክሮዎች ትምህርት በመውሰድ፣ ምክክር ወደ መግባባት ሊያደርስ የሚችል አዋጭ መንገድ እንደሆነ በመገንዘብ መንግሥት እርምጃ እንዲወስድ አበረታተዋል፤ ጠይቀውማል፡፡
ይህ ሂደት በተለይም በታኅሣሥ ወር 2014 ዓ.ም በሀገሪቱ የምክክርን መሠረት በመጣል ረገድ አንድ እርምጃ ተራመደ፡፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን በማቋቋም የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን እንዲመራና እንዲያስተባብር ኃላፊነት ሰጠው።
የኮሚሽኑ አመሠራረት በራሱ የሕዝብ ተሳትፎን ባማከለ መልኩ የተቃኘ ነበር፡፡ ከሕዝብ በቀረበው ጥቆማ መሠረት 632 ዕጩዎች ለኮሚሽነርነት ተጠቁመው፣ 42ቱ በዕጩነት ከተመረጡ በኋላ፣ በመጨረሻም 11 ኮሚሽነሮች ተመርጠው ተቋሙን እንዲመሩ ቃለ መሐላ ፈጸሙ።
የሂደቱን መሠረት መጣል
የኮሚሽኑ የመጀመሪያ ተግባር በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በአንድ አዳራሽ ውስጥ መሰብሰብ አልነበረም፡፡ ይልቁንም የምክክር ሂደቱ ትርጉም ያለው እንዲሆን መደላድል መፍጠር ነበር፡፡
በመሆኑም ኮሚሽኑ በመጀመሪያ ሥራው እጅግ መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያሉ የአለመግባባት መንስኤዎችን ለመለየት፣ እነማን መሳተፍ እንዳለባቸው ለመወሰን እና ኢትዮጵያውያን ለምክክር የሚሆኑ ጉዳዮችን በማዋጣት ረገድ እንዴት አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚችሉ የሚያስችል ሥነ-ዘዴ አዘጋጀ፡፡
በሂደቱ በወረዳ ደረጃ ከሚገኙ ማኅበረሰብ ክፍሎች ጀምሮ እስከ ፖለቲካና የሐሳብ መሪዎች፣ የመንግሥት ተቋማት፣ ማኅበራት እና በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በማካተት የሰፊ ባለድርሻ አካላት ስብስብን ለየ፡፡
በክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የተካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ከፖለቲካ እና ከተቋማት ወሰን የተሻገረ እንዲሆን ተደርጎ የተቃኘ ነበር፡፡
የአርሶ/አርብቶ አደር ተወካዮች፣ የንግዱ ማኅበረሰብ፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ ዕድሮች፣ የማኅበረሰብ መሪዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ መምህራን፣ በባህል እና በሙያቸው ምክንያት የተገለሉ እንዲሁም ተፈናቃዮች በክልል እና በከተማ አስተዳደር ደረጃ በተካሄዱ ሂደቶች ተሳታፊዎች ሆነዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመንግሥት ተወካዮች፣ ተቋማት እና ታዋቂ ግለሰቦችም እንደ ቁልፍ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊዎች ሆነዋል፡፡
በፌዴራል ደረጃ 38 የባለድርሻ አካላት ቡድኖች በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ የነቃ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ በዚህ ሂደት በተለይም የሃይማኖት ተቋማትን፣ ዲሞክራሲ ተቋማትን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የሲቪል ማኅበራትን፣ የመንግሥት አካላትን፣ ሀገር አቀፍ ማኅበራትን፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን እና የሚዲያ ተቋማትን የወከሉ ወኪሎች ተሳታፊዎች ሆነዋል፡፡
በሌላ በኩል ኮሚሽኑ በአፍሪካ፣ ሰሜን አሜሪካ፣ መካከለኛው ምሥራቅ እና አውሮፓ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አጀንዳ አሰባስቧል፡፡
ሀገራዊ አጀንዳ መቅረጽ
የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራው እንደተጠናቀቀ ኮሚሽኑ የሰበሰባቸውን አጀንዳዎች መቅረጽ እና ለምክክር ሂደቱ የማዘጋጀት ሥራ አከናወነ፡፡
ይህንን ተከትሎ ረቂቅ አጀንዳዎች ለሃይማኖት ተቋማት፣ ለሲቪክ ማኅበራት፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለመንግሥት አካላት፣ ለምሁራን እና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ግብዓት እንዲሰጡባቸው ቀርበው ሁሉም አካላት የበኩላቸው አበርክተዋል፡፡
ይህ ሂደት የተቀረጹ የምክክር አጀንዳዎችን ለማጥራት ብቻ ሳይሆን፣ ባለድርሻ አካላት ሐሳቦቻቸው በሂደቱ ውስጥ መንጸባረቃቸውን በማረጋገጥ ወደ ሀገራዊ መግባባት ሊያደርሱ የሚችሉ ርዕሰ ጉዳዮችን በመቅረጽ ረገድ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ዕድል ሰጥቷል፡፡
ኢትዮጵያውያንን ወደ ምክክር መድረክ ማሰባሰብ
ከየወረዳው ከሚገኙ ማኅበረሰብ ክፍሎች፣ ከክልል እና ከተማ አስተዳደሮች ባለድርሻ አካላት፣ ከፌዴራል ባለድርሻ አካላት እና ከዲያስፖራው የተውጣጡ 4,000 ኢትዮጵያውያን ተሳታፊዎች በአንድ ላይ ለመመካከር ተሰባሰቡ፡፡
እነዚህ ተሳታፊዎች ኮሚሽኑ ቀደም ሲል አጀንዳዎችን ካሰባሰበባቸው አካላት እና ባለድርሻ አካላት የተመረጡ ወይም የተወከሉ ሲሆኑ ይህም በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን ውክልና ከቀደሙት የምክክር ሂደቶች ጋር በአግባቡ ያጣመረ ነበር፡፡
የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ዓላማ ኢትዮጵያውያን እጅግ መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮቻቸው ላይ የሚመካከሩበት፣ የተሻለ መግባባትን የሚያጎለብቱበት፣ የጋራ መግባባት የሚደረስባቸውን አቅጣጫዎች የሚለዩበትን መድረክ መፍጠር ነበር፡፡
በጥቅሉ ሂደቱ ምክክርን የአለመግባባቶች መፍቻ የማዕዘን ድንጋይ የማድረግ ጥረት ነበር፡፡
ምክክርን ማዕከል ያደረጉ ሐሳቦች
የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ የተጀመረ ሲሆን ሂደቱ 4,000 ተመካካሪዎችን ከሁሉም የሀገራችን እና የዓለማችን ክፍሎች ማሰባሰብ ችሏል።
በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ምክክር የሚደረግባቸው ስምንት ሀገራዊ አጀንዳዎች የተለዩ ሲሆን እያንዳንዱ 500 አባላት ያሉት ተመካካሪ ቡድን በአንድ አጀንዳ ላይ ሲመካከር ሰንብቷል፡፡
ጉባኤው የተመራበት ሥነ-ዘዴም ተመካካሪዎች የመናገር፣ የመደማመጥ እና የመግባቢያ ነጥቦችን የመለየት ዕድል እንዲኖራቸው በሚያስችል መልኩ ነበር።
ከዚህ ባሻገር የምክክር ሂደቱ 10 አባላት ባሏቸው ትንንሽ ቡድኖች ተጀምሮ፣ 50 አባላት ወዳሏቸው ንዑሳን ቡድኖች፣ በመቀጠልም 250 አባላት ወዳሏቸው ስልታዊ ቡድኖች አድጓል።
በምክክር ሂደቱ የቀረቡ ምክረ-ሐሳቦች ከላይ በተጠቀሱት መንገዶች ምክክር ተደርጎባቸው ከተጣሩ በኋላ የተጠቃለሉ ምክረ-ሐሳቦች 500 አባላት ባሉት የአጀንዳ ተመካካሪ ቡድን ቀርበው ጸድቀዋል።
እያንዳንዱ ተመካካሪ ቡድን በመጨረሻም በተለያዩ አጀንዳዎች መካከል የቀረቡ ምክረ-ሐሳቦችን ማጣጣም (cross-validation) ለማካሄድ 15 ተወካዮችን መርጧል፡፡
በዚህ መሠረት በአጠቃላይ 120 የሚሆኑ የምክረ-ሐሳብ አቀናጆች ተመርጠው ሥራቸውን በአግባቡ አከናውነዋል፡፡
በሂደቱ ምክረ-ሐሳቦችን የማጣጣም ዋነኛ ዓላማም በተለያዩ ተመካካሪ ቡድኖች ውስጥ የተነሱ ምክረ-ሐሳቦች እርስ በእርስ እንዳይጣረሱ እና አላስፈላጊ ድግግሞሽ እንዳይኖር በማሰብ ነበር፡፡
ይህ ጉባኤ ስኬታማ ይሆን ዘንድ በተለያዩ ዘርፎች ሙያዊ እገዛ ያደረጉ ባለሙያዎች መኖራቸው ሊዘነጋ አይገባም።
80 የባለሙያዎች ቡድን ለተሳታፊዎች በአጀንዳዎቹ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል፤ ይህም ተሳታፊዎች መረጃን ማዕከል ያደረገ ምክክር እንዲያደርጉ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡
ከዚያ በተጨማሪ 160 የሚጠጉ አመካካሪዎች የምክክሩን ሂደት የመሩ ሲሆን፣ 158 ቃለ-ጉባኤ አዘጋጆች በእያንዳንዱ የምክክር ሂደት ውስጥ የነበሩ ምክረ-ሐሳቦችን በመሰነድ ለሂደቱ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
ከመግባባት ያለፈ ሀገራዊ ምክክር
የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ፋይዳ ምክረ-ሐሳቦችን በመግባባት ማዘጋጀት ብቻ አልነበረም። ከዚያ በተጨማሪ የተለያየ ልምድ፣ ፍላጎት እና የፖለቲካ አቋም ያላቸው ሰዎች እርስ በእርስ በቀጥታ የሚነጋገሩበትን መድረክ መፍጠርም ጭምር ነበር፡፡
ይህ መድረክ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ውስጥ ትልቅ ሽግግርን ያመለክታል፦ የሂደቱ ግብ “ማን አሸነፈ፣ ማን ተሸነፈ?” ከሚለው ኋላ ቀር እሳቤ ይልቅ ወደ “በምን ላይ መስማማት እንችላለን? ምን ዓይነት ልዩነቶችን ማስተናገድ ይቻላል? እና በአንድነት ምን ዓይነት የጋራ ተስፋ መገንባት እንችላለን?” ወደሚለው ጥያቄ መሸጋገር ነው፡፡
የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት
ነሐሴ 16 ቀን 2018 ዓ.ም በተካሄደው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴን ጨምሮ ጥሪ የተደረጋላቸው የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገራት የክብር እንግዶች ተገኝተው የተለያዩ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል፡፡ በመድረኩ ላይ ፕሬዚዳንት ታዬ እንደተናገሩት ሀገራዊ ምክክሩ አንድነትን የሚያጠናክር ትልቅ የታሪክ ምዕራፍ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል በክብር እንግድነት የተገኙት የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተወጣጡ ወኪሎች እርስ በእርስ ለመግባባት ያሳዩትን ተነሳሽነት አድንቀው ይህም ዜጎች በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ ለመነጋገር ፈቃደኛ ሲሆኑ የበለጠ ፍሬያማ እንደሚሆን አውስተዋል፡፡
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ምክክር የሀገሪቱን ፈተናዎች ለመፍታት የሚያስችል አቅም ያለው መንገድ መሆኑን ጠቁመው ኢትዮጵያ በምክክር ልትፈታው የማትችለው ምንም ዓይነት ፈተና እንደሌለ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ አክለውም በኃይል አማራጭ አሸናፊ የሚሆን አካል እንደማይኖር ገልጸው ምክክር ሁሉንም አሸናፊ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡
ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረሥላሴ በበኩላቸው የሀገራዊ ምክክሩ መጠናቀቅ በኢትዮጵያ የፖለቲካ እና የማኅበራዊ ጉዞ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ አክለውም ሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያውያን ለረጅም ጊዜ የቆዩ ቅሬታዎችን፣ የፖለቲካ ልዩነቶችን እና የታሪክ ክፍፍሎችን ከግጭት ይልቅ በምክክር እንዲፈቱ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የነገው መንገዳችን
የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ከአንድ ወቅት ክስተት ባለፈ የሚሻገሩ ታላላቅ ግቦች አሉት፡፡ በዚህ ሂደት የሚጠበቁ ውጤቶች መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባትን መፍጠር፣ ሀገራዊ አንድነትን እና ማኅበራዊ ትስስርን ማጠናከር፣ የመፍትሔ ሐሳቦች የሕዝብ ባለቤትነት እንዲኖራቸው ማድረግ፣ በተለያዩ ማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል እምነትን መገንባት እና ለዘላቂ ሰላም፣ ለዲሞክራሲያዊ አስተዳደር እና ለሀገር ግንባታ መሠረት መጣልን ያካትታሉ፡፡
የሀገራዊ ምክክር ጉዞ ረጅም ነበር። ተቋም መፍጠርን፣ ሥነ-ዘዴን ማዘጋጀትን፣ ባለድርሻ አካላትን መለየትን፣ አጀንዳ ማሰባሰብን፣ የሕዝብ ተሳትፎን ማጎልበት፣ ውክልናን ማረጋገጥ፣ አጀንዳን መቅረጽን እና በሀገር አቀፍ ደረጃ የምክክር ጉባኤ ማካሄድን ጠይቋል፡፡
በሀገራችን ኢትዮጵያ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በአንድነት መቀመጥ፣ መደማመጥ እና የጋራ መግባባትን መፈለግ በራሱ ትልቅ እርምጃ ነው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የኢትዮጵያ ልጆች ሀገራዊ ችግሮችን በምክክር መፍታት እንደሚችሉ ያስመሰከሩበት መድረክ ነው።
በምክክር ሁሉም አሸናፊ ነው!