የኢትዮጵያ እያደገ የመጣው የኃይል አቅም ለቀጣናዊ ትስስርና ትብብር አዳዲስ ዕድሎችን ከፍቷል-ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር )

You are currently viewing የኢትዮጵያ እያደገ የመጣው የኃይል አቅም ለቀጣናዊ ትስስርና ትብብር አዳዲስ ዕድሎችን ከፍቷል-ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር )

AMN ነሐሴ 20፣ 2018 ዓ.ም.

የአባይ ወንዝ ለኢትዮጵያ የልማት ዕቅድ፣ የሀገራዊ ሉዓላዊነት እና የቀጣናዊ ትብብር ራዕይ ማዕከላዊ ሚና አለው።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ለማፋጠን፣ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማስፋት፣ ንግድን ለማሳደግ እና በአባይ ተፋሰስ ሀገራት መካከል የበለጠ ትስስርን ለማስፋት ለተያዘው ራዕይ ዋና ምሰሶ ነው።

የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ) ከPulse of Africa ጋር ባደረጉት ልዩ ቃለ ምልልስ፣ ኢትዮጵያ የአባይ ተፋሰስን ዋና ዋና ገባር ወንዞቿን እንደ ተከዜ፣ ባሮ እና አባይን ለልማት ለመጠቀም ስላደረገችው የረጅም ዘመናት ጥረት አብራርተዋል።

ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ቀደምት ትውልዶች የሀገሪቱን ሰፊ የውሃ ሀብት በመጠቀም ሀገሪቱን ለማልማት የረጅም ጊዜ ሕልም ነበራቸው።
ይህንን ራዕይ ለማሳካትም በርካታ የልማት፣ የአካባቢ ጥበቃ እና የማኅበራዊ መሠረተ ልማት ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንቶች ተደርገዋል።

ቀደምት መንግሥታትም የኢትዮጵያን የውሃና የኃይል ሀብት ለማልማት ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም፣ የውጭ ጫናዎችና ሌሎች ተግዳሮቶች ብዙዎቹ ፕሮጀክቶች በሀገሪቱ ምኞት መሠረት እንዳይሰሩ እንቅፋት ሆነዋል ብለዋል።

ዛሬ ግን ኢትዮጵያ በራሷ ሀብትና በዜጎቿ አስተዋጽኦ የተገነባውን በአፍሪካ ትልቁን የውሃ ኃይል ማመንጫ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በመገንባቷ ኩራት ይሰማታል።

እንደ ሚኒስትር ሀብታሙ ገለጻ፣ የህዳሴ ግድብ የሀገራዊ አንድነት ምልክት ሆኗል።

ግድቡ ሙሉ በሙሉ ለኤሌክትሪክ ማመንጫ የተነደፈ ሲሆን፣ በአባይ ላይ መገንባቱም ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን ለአካባቢው ሰፊ ብልጽግና በሚያበረክት መንገድ ለመጠቀም ያላትን ዓላማ የሚያሳይ መሆኑን አስረድተዋል።

እንዲህ ያለ ግዙፍ ግድብ በተለይም ከፍተኛውን የውሃ መጠን በምናበረክትበት ወንዝ ላይ መገንባት፣ የመላው ቀጣና ብልጽግናን ለማምጣት ተገቢውን አቅጣጫ መከተል ማለት ነው።

በዚህ ግድብ ኢትዮጵያ ብቻ ተጠቃሚ አይደለችም፤ በአባይ ተፋሰስ ያሉ ወንድሞቻችንና ጎረቤቶቻችንም ይጠቀማሉ” ብለዋል።

በመስከረም 2017 ዓ.ም የህዳሴ ግድቡ ከተመረቀ በኋላ፣ ኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው ኤሌክትሪክ ማመንጨት መቻሏን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የሚመነጨው ኃይልም የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ለማሟላት ብቻ ሳይሆን፣ የኤሌክትሪክ ፍላጎታቸው እየጨመረ የመጣውን ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ እና ሌሎች ጎረቤት ሀገራትን ለመደገፍም ያገለግላል ብለዋል።

ሚኒስትሩ የህዳሴ ግድብ ጥቅም ከኢትዮጵያ ድንበር የሚያልፍ መሆኑን በማስገንዘብ፣ የግድቡ ቀጠናዊ ተጽዕኖ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንቶች ሰፊ የኢኮኖሚና የልማት ጥቅም ሊያስገኙ እንደሚችሉ ጠቃሚ ምሳሌ መሆኑን ጠቁመዋል።

“ከጎረቤቶቻችን ጋር ከምንፈጥራቸው የኃይል ግንኙነቶች ባሻገር፣ ሌላው ጥቅም የውሃ ኃይል አረንጓዴ የኃይል ምንጭ መሆኑ ነው” ብለዋል።

የውሃ ኃይል ንጹህና ታዳሽ የኃይል ምንጭ በመሆኑ፣ በዓለም ዙሪያ ሀገራት ከቅሪተ አካል የነዳጅ አማራጭ የሆኑ የኃይል ምንጮችን ለመፈለግ፣ ብክለትንና የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ በሚያደርጉት ጥረት የውሃ ኃይል እየጨመረ የመጣ ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል።

እንደ ሚኒስትር ሀብታሙ ገለጻ፣ ኬንያ ኢትዮጵያ አሁን ልታቀርብ ከምትችለው መጠን በላይ ኤሌክትሪክ እየፈለገች መሆኗ በቀጠናው የተረጋጋ የኃይል አቅርቦት ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ያሳያል።

ሶማሊያና ደቡብ ሱዳንም ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው፣ ሆኖም ከእነዚህ ሀገራት አንዳንዶቹ እስካሁን ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኔትወርክ ጋር እንዳልተገናኙ ጠቁመዋል።

ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ማመንጫ አቅም ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ በእጥፍ አድጓል።

ቀደም ሲል የሀገሪቱ የማመንጨት አቅም 4.6 ጊጋዋት፣ ወይም 4,600 ሜጋዋት ገደማ ነበር። አሁን ግን ወደ 10 ጊጋዋት እየተቃረበ መሆኑን ገልጸዋል።

“ይህ የኃይል ማመንጫ አቅም ተረጋግጧል፤ ለኢትዮጵያውያንም ሆነ ለጎረቤቶቻችን እየዋለ ነው” ብለዋል ሚኒስትር ሀብታሙ።

ኢትዮጵያ እያሳደገች ያለችው የኃይል አቅም ለአገሪቱ የኢኮኖሚ ለውጥ ብቻ ሳይሆን፣ በአፍሪካ ቀንድ እና በሰፊው የናይል ተፋሰስ አካባቢ የተሻለ የቀጣናዊ ትስስር፣ ንግድ እና ትብብር ለማጠናከር እድሎችን እየፈጠረ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

በብርሃኑ ወርቅነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review