AMN- ነሐሴ 21/2018 ዓ.ም

የሰው ልጅን ሙሉ እንቅስቃሴ፣ አስተሳሰብና ስሜት በመቆጣጠር ረገድ የነርቭ ሥርዓት የሚጫወተው ሚና እጅግ የላቀ ነው።
አንጎልን፣ የአከርካሪ አጥንትን እና መላው የሰውነት ነርቮችን ያካተተው ይህ ሥርዓት፣ መልእክቶችን ከአእምሮ ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች በማስተላለፍ የሰውነትን ተፈጥሯዊ ሚዛን እንደሚጠብቅ ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉት የኒውሮ ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ሀናንያን ጂባይ ይገልፃሉ።
ለነርቭ ሥርዓት መዛባትና ጉዳት የዘረ-መል ተጽዕኖዎች፣ የሰውነት የበሽታ ተከላካይ ሥርዓት መዛባት እና የባክቴሪያ ወይም የቫይረስ ኢንፌክሽኖች ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን ዶክተር ሀናንያን ያብራራሉ።

ድንገተኛ አደጋዎች፣ የደም ዝውውር እጥረት፣ ለመርዛማ ኬሚካሎች መጋለጥ፣ የቫይታሚን ቢ እጥረት እና ከአቅም በላይ የሆነ የአልኮል መጠጥ መጠቀም ለችግሩ እንደሚዳርጉም ይናገራሉ።
ምንም እንኳን ሕመሙ በማንኛውም የዕድሜ ክልል ላይ ሊከሰት ቢችልም፣ በተለይም ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ በሆኑ አረጋውያን ላይ በብዛት እንደሚስተዋል ስፔሻሊስቱ አስገንዝበዋል።
የነርቭ ሥርዓት መታወክ ሲያጋጥም የጡንቻ ድክመት፣ መንቀጥቀጥ፣ እና የሰውነት ሚዛንን የመጠበቅ ችግር እንደሚታይም ነው የገለጹት።
እንዲሁም በእጅና በእግር ላይ የሚሰማ መደንዘዝ፣ የመወጋት ወይም የመቃጠል ስሜት፣ የመስማት፣ የመናገር፣ የመዋጥ ወይም የመተንፈስ ድንገተኛ መዛባትም ይከሰታል።

የማስታወስ ችሎታ ማጣት፣ ከፍተኛ ግራ መጋባት፣ የማያቋርጥ ከባድ ራስ ምታት፣ ያለ በቂ ምክንያት የሚከሰት ከፍተኛ ድካም እና የንቃት ደረጃ መቀነስ የሕመሙ ተጨማሪ ምልክቶች እንደሆኑም አስረድተዋል።
በሽታውን ሙሉ በሙሉ መከላከል አስቸጋሪ ቢሆንም፣ አዘውትሮ አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግ፣ በቀን ከ6 እስከ 8 ሰዓት በቂ እንቅልፍ በማግኘት እና በአትክልትና ፍራፍሬ የበለጸገ ምግብ በመመገብ የሕመሙን ስጋት መቀነስ እንደሚቻልም ይጠቁማሉ።
ከዚህ በተጨማሪ ከአልኮልና ከትምባሆ ሙሉ በሙሉ በመቆጠብ እንዲሁም እንደ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ የስኳር በሽታ እና የኮሌስትሮል መጠን ያሉ ተዛማጅ የጤና እክሎችን በመከታተል ራስን መጠበቅ ይገባል።
ሕመሙ በምርመራ ከተረጋገጠ በኋላ እብጠትን የሚቀንሱ፣ ሕመምን የሚያስታግሱና የነርቭ ሴሎችን ተግባር የሚያሻሽሉ መድኃኒቶችን መውሰድ እንደሚገባ ዶ/ር ሀናንያን አብራርተዋል።
በፊዚዮቴራፒና በንግግር ቴራፒ የሰውነት እንቅስቃሴንና የመናገር አቅምን ማሻሻል የሚቻል ሲሆን፣ በአደጋ የተጎዱ ነርቮችን ለመማነቃቃት ወይም በውስጥ የሚበቅሉ ዕጢዎችን ለማስወገድ በቀዶ ሕክምና መታገዝ እንደሚገባም አስረድተዋል።
በበረከት ጌታቸው