AMN – ነሐሴ 22/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትውልድን በዕውቀት፣ በክህሎትና በሥነ-ምግባር ለማነጽ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዘላለም ሙላቱ ገለጹ።
ኃላፊው ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳመለከቱት፤ የከተማዋ የትምህርት ሥርዓት አደረጃጀት፣ ስርጭት እና ውጤት አብዛኛውን ማኅበረሰብ ያካተተ እንዲሆን ሰፊ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
ትምህርት ለአንድ ሀገር ዕድገትና ብልጽግና ትልቁን ሚና የሚጫወትና የብዙ ነገሮች መክፈቻ ቁልፍ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ዘላለም፣ የትምህርት ሥርዓቱ ተደራሽ፣ ጥራቱን የጠበቀ እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ መሆን እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።
በከተማዋ የሚገኙ የትምህርት ተቋማት ለነገዋ ሀገር መሠረት የሚጥል ትውልድ ለማፍራት በሚያስችል ቁመና ላይ እንዲገኙ የማድረግ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም አብራርተዋል።
«ትውልድን መገንባት ከሁሉ በላይ ይበልጣል» በሚል መሪ ሀሳብ፣ ተማሪዎች በድህነትና በገቢ ማነስ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው እንዳይነጠሉና ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል ሰፊ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ኃላፊው አውስተዋል።
በዚህም አነስተኛ ገቢ ካላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ለሚመጡ ተማሪዎች የዩኒፎርም፣ የምግብ እና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፎችን በማድረግ ትምህርታቸውን ያለ ምንም ሥጋት እንዲከታተሉ መደረጉን ገልጸዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የትምህርት ዘርፉን ለማዘመን የሚያስችል ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ የትምህርት ጥራትንና ፍትሃዊነትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።
በወርቅነህ አቢዮ