AMN – ነሐሴ 22/2018 ዓ.ም
የ76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ኮሚቴ ጉባኤ ተሳታፊ የተለያዩ ሀገራት የጤና ሚኒስትሮች የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን ጎብኝተዋል።
ጎብኝዎቹ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ላይ እንዲህ ያለ የዕድገት ደረጃ በአፍሪካ ውስጥ አይተው እንደማያውቁ ገልፀው ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ከኢንስቲትዩቱ ብዙ የሚማሩት ነገር እንዳለ አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በአስደናቂ ሁኔታ አቅሟን አሳይታለች ያሉት የጤና ሚኒስትሮቹ ፤ ኢንስቲትዩቱ የሚሰራቸው የፈጠራ ሥራዎች ራዕዩን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር ታዬ ግርማ (ዶ/ር) በጤና ፣ በግብርና እና በሌሎች ዘርፎች እየተመዘገበ ያለውን የምርምርና ልማት ስኬት አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በገለጻቸው ኢንስቲትዩቱ የአፍሪካ የልህቀት ማዕከል እንደመሆኑ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ግዙፍ ዳታ ሴንተር በመገንባት ለተለያዩ ተቋማት እየሰጠ ያለው የክላውድ አገልግሎት፣ ስለ ኤአይ ብሔራዊ ፖሊሲ፣ ለስታርታፖች ስለሚደረገው ድጋፍ ለጎብኚዎቹ ማብራሪያ መሰጠቱን ከኢንስቲትዩቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡