የምንሰራው ከልብ ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN- ነሐሴ 21/2018 ዓ.ም

ህዝባችንን ለማገልገል ቃላችንን በተግባር እየፈጸምን፣ የተናገርነውን በተጨባጭ እያቀረብን የምንሰራው ከልብ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመዲናዋ አራት ዘመናዊ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ተርሚናልና የንግድ ማዕከል እንዲሁም ፕላዛ ምረቃ ሥነ-ስርዓት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በአዲስ አበባ ከተማ ከለውጡ ወዲህ በትራንስፖርት ዘርፍ ታሪካዊና መሰረታዊ ለውጦች መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህም ለህዝባችን የምናቀርበው ባዶ ፕሮፓጋንዳ ሳይሆን፣ ተጨባጭ ስራዎችን ሰርተን ተጠቃሚ የምናደርግበት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ከለውጡ በፊት 3 ሺህ ብቻ የነበረውን የአንድ ጊዜ የተሽከርካሪ ማቆሚያ አቅም እና ምንም ያልነበረን ተርሚናል በአሁኑ ጊዜ በጥራትና በፍጥነት የተገነቡ፣ ዘመናዊ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎችን እና ተርሚናሎችን ከ170 ሺህ በላይ ማድረስ ችለናል ብለዋል።

በተዘረጉት ዘመናዊ የፓርኪንግ ስራዎች ብቻ ከ20 ሺህ በላይ ወጣቶች መሠማራታቸውን፣ እንዲሁም በፓርኪንግ ቦታዎች ላይ በተገነቡ ሱቆች፣ ካፌዎች እና ፕላዛዎች ተጨማሪ ሰፊ የስራ እድሎች መፈጠራቸውን ከንቲባዋ ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ቀደም መንገዶች ለእግረኛ፣ ለተሽከርካሪ፣ ለፓርኪንግ እና ለንግድ በአንድ ላይ ይጨናነቁ እንደነበር በማስታወስ፣ አሁን ላይ የተገነቡት ዘመናዊ ተርሚናሎችና ማቆሚያዎች የነዋሪዎችን ማህበራዊ መስተጋብር ማጠናከራቸውን እና ለሰዎች ክብር የሚመጥን አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።

የተከናወኑት ስራዎች የከተማዋን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ አሟልተዋል ማለት እንዳልሆነ እና አዲስ አበባ ከዚህ በላይ እንደሚገባትም ከንቲባዋ አጽንዖት ሰጥተዋል።

በመሆኑም መሰረተ ልማቶቹን ከማዕከል ወደ ዳር እና ወደየሰፈሩ በማድረስ የህዝቡን ፍላጎት በዘላቂነት ምላሽ ለመስጠት የከተማ አስተዳደሩ አበክሮ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

ይህ የተመዘገበው ለውጥ የከተማዋን ነዋሪዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ከመደገፉም ባሻገር፣ አዲስ አበባን ለኑሮ ምቹና ተወዳዳሪ ከተማ ለማድረግ የሚያስችል አበረታች ምዕራፍ መሆኑም አመላክተዋል።

በፍሬሕይወት ብርሀኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review