AMN- ነሐሴ 22/2018 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ስፖርት እንቅስቃሴ ውስጥ “ዓድዋ ፋይት ናይት” የሚክስድ ማርሻል አርት (MMA) ውድድር አዲስ ምዕራፍ እየከፈተ ይገኛል፡፡
እምብዛም ሰፊ እውቅና ያልነበረው ይህ የስፖርት ውድድር ዘርፍ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ከፍተኛ ተቀባይነት እና ተወዳጅነት እያገኘ መጥቷል፡፡
የሚክስድ ማርሻርል አርት ወጣቱ በስፖርት እንዲዳብር ብቻ ሳይሆን ለቱሪዝም እድገት ያለው ፋይዳም ከፍተኛ ነው፡፡
ሀገራት ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኙ እንዲሁም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴያቸው እንዲነቃቃ ጉልህ ሚና ይጫወታል።
እንደ አልቲሜት ፋይቲንግ ሻምፒዮንሺፕ(ዩ ኤፍ ሲ) ፣ ዋን ሻምፒዮንሺፕ ፣ ፕሮፌሽናልስ ፋይተርስ ሊግ(ፒ.ኤፍ.ኤል) ያሉት በአለም ታዋቂዎቹ የሚክስድ ማርሻል አርት ውድድሮች ሲሆኑ ፍልሚያዎቹን ለመመልከት ከፍተኛ ሕዝብ የሚጎርፍባቸው ናቸው፡፡
እነዚህ ውድድሮች ለቱሪዝም መነቃቃት የሚፈጥሩት አቅም እጅግ ላቅ ያለ ነው፡፡ ለምሳሌ የመጀመሪያው አልቲሜት ፋይቲንግ ሻምፒዮንሺፕ(ዩ ኤፍ ሲ) ውድድር ሲካሄድ 67 በመቶዎቹ ከሌላ አካባቢ ለውድድሩ የተጓዙ እንደነበር ይጠቀሳል፡፡
የቲኬት ሺያጭ ፣ ከመስተንግዶ የሚገኝ ገቢ ፣ የሆቴል አገልግሎት በሚሊየን የሚቆጠሩ ገንዘቦችን ለአካባቢው ያስገኛሉ፡፡

መሰል ውድድሮች ሐገራት ተቀባይነታቸውንና ተፅእኖ ፈጣሪነታቸውን ለማሳደግም ይጠቀሙባታል፡፡ ታይላንድ ሞይ ታይ ስፖርትን በመጠቀም ድህረ ኮቪድ የቱሪዝም ገቢዋን ለማሳደግ ስትራቴጂ ነድፋ ሰርታለች፡፡
አርጀንቲና፣ ካዛኪስታን፣ ኮሎምቢያ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጀርመን እና ብራዚል ታላላቅ የዓለም የቦክስ ሻምፒዮና ውድድሮችን በማስተናገድ ዓለም አቀፍ ቱሪስቶችን ይስባሉ።
በኢትዮጵያም በፈጣን ሁኔታ እየተነቃቃ የሚየገኘው የሚክስድ ማርሻል አርት ፍልሚያ በብዙዎች ዘንድም ተወዳጅ እየሆነ ይገኛል፡፡ በዚህ ረገድ ዓድዋ ፋይት ናይት በኢትዮጵያ ስፖርት ውስጥ አዲስ ታሪክ እየጻፈ ይገኛል፡፡
ትናንት በዓድዋ ድል መታሰቢያ የተደረገው 2ተኛው “ዓድዋ ፋይት ናይት” የሚክስድ ማርሻል አርት(MMA) ውድድር በደመቀ ድባብ ተጠናቅቋል፡፡
ውድድሩ ከኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እንዲሁም ከጎረቤት ሀገር ጭምር ተፈላሚዎችን በአንድ መድረክ ያሰባሰበ ሲሆን ፣ በርካታ የስፖርት አፍቃሪያንን ትኩረት አግኝቷል፡፡
አዲስ አበባ ለስፖርት ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት የተለያዩ ውድድሮችን ለማካሄድ የሚያስችሉ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ የስፖርት ማዕከላትን መገንባቷ ለዚህ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡
ይህ ከተማዋ የስፖርት ውድድሮች ማዕከል እንድትሆን የጎላ አስተዋጽኦ የሚያበርከት ነው፡፡
ቀደም ሲል በአትሌቲክስና በሳይክል አለም አቀፍ ውድድሮችን ያስተናገደችው አዲስ አበባ ፣ በሚክስድ ማርሻል አርት ውድድርም የዓለም ትኩረት እንደምትሆን የዓድዋ ፋይት ናይት ተስፋ የሚፈነጥቅ ነው፡፡
ይህም አዲስ አበባ የስፖርት ቱሪዝም አንዷ መዳረሻ እንድትሆን እንደሚያስችል ይታመናል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሰል የስፖርት እንቅስቃሴዎችን ለመደገፍ የተዘጋጀ አመራር መኖሩም ለውጤታማነቱ ወሳኙን ሚና ይጫወታል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በትናንትናው የዓድዋ ፋይት ናይት ውድድር ላይ ተገኝተው ወጣቶችን በማበረታት ይህን አቋም በተግባር አረጋግጠዋል፡፡
በየሻምበል ምህረት