የሳቅ ድግስ – በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ

AMN-ነሐሴ 22/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብና የኮሜዲ መድረክ ላይ ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ ስሙን በደማቅ ቀለም የጻፈው ኮሜዲያን እና ተዋና የብዙዎችን ልብ በሳቅና በደስታ ያሞቀ አንቱ የተባለ የጥበብ ሰው ነው ኮሜዲያን ደረጄ ሀይሌ።

በተለይም ከረጅም ጊዜ የሙያ አጋሩ ከኮሜዲያን ሀብቴ ምትኩ ጋር በመሆን ያቀረቧቸው አዝናኝና ማህበራዊ ህይወትን የሚዳስሱ ድንቅ የኮሜዲ ስራዎች በበርካታ የሃገራችን ተመልካቾች ዘንድ የማይረሳ ቦታ አላቸው።

ከኮሜዲያነ‍እ ሀብቴ ምትኩ ጋርም ” ደረጀና ሀብቴ ” የሚለውን የጋራ ስም ( ብራንድ ) በመፍጠር ባቀረቧቸው የተለያዩ አዝናኝ እንዲሁም አስተማሪ የኮሜዲ ስራዎቸን ዝናን ማትረፍ ችለዋል።

ደረጄ ሀይሌ በቴአትር፣ በፊልም እና በኮሜዲ ስራዎች ውስጥ በከፍተኛ የትወና ክህሎቱ የሚታወቅ ሲሆን የመድረክ እና የቲ.ቪ ኮሜዲዎችን በተጨማሪም ህብረተሰቡን እያዝናኑ የሚያስተምሩ በርካታ ስታንድ-አፕ ኮሜዲዎችን እና የአጭር ድራማ ስራዎችን አበርክቷል።

ከነዚ የትወና እንዲሁም የስታንዳፕ ኮሜዲ ስራዎቹ በተጨማሪም “ትዝታ ሲጨለፍ” ፣ “አንዳንድ ነገሮች እና ሌሎች” ፣ “የሚልየነሩ ፍዳ “ የተሰኙ መፅሀፍቶችንም ፅፎ ለአንባቢዎች ያበቃ የጥምር ሙያ ባለቤት ነው።

ይህ የጥበብ ባለቤት አሁንም አዲስና አዝናኝ ይዘት ይዞ ወደ ተመልካች ሊቀርብ ዝግጅቱን ጨርሷል! ኮሜዲያን ደረጄ ሀይሌ በቅርቡ በአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ “የጥበብ ጨዋታ” የተሰኝ አዲስ የቴሌቪዥን ሾው ይዞ ብቅ ሊል ነው።

ፕሮግራሙ የኪነ-ጥበብን፣ የመዝናኛን እና የጨዋታን ድባብ አዋህዶ የሚያቀርብ ሲሆን፣ ደረጄ በሙያ ልምዱ እና በተፈጥሮ ሳቁ እንዲሁም ቀልዶቹ የታጀበ አዲስ የመዝናኛ ፕሮግራም ለተመልካች ያደርሳል።

“የጥበብ ጨዋታን“ በአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ በአዲስ አመት ይዞ ለመምጣት ሽርጉዱን ጨርሷል።

በሔዋን ታዬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review