AMN – ነሐሴ 24/2018 ዓ.ም

ከንቲባ አዳነች አበቤ በመዲናዋ ባለፉት አምስት ዓመታት የተመዘገቡ ውጤቶችን መሠረት በማድረግ፣ በቀጣዩ የዕቅድ ዘመን የሕዝቡን አደራ ለመወጣት ከመቼውም ጊዜ በላይ በትጋት እንደሚሰራ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቀጣይ አምስት ዓመታት ስትራቴጂካዊ እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ የተዘጋጀው የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ አዳነች አበቤ፤ ባለፉት ዓመታት ከሕዝቡ የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት በርካታ ስትራቴጂክዊ ዕቅዶች መተግበራቸውን አስታውሰዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት በተከናወኑ ሥራዎች መዲናዋ ተወዳዳሪ እንድትሆን እና ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉን ከንቲባዋ ገልጸዋል።
የከተማው ነዋሪ ላሳየው እምነትና ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት ከንቲባዋ፤ ሕዝቡ የጣለውን አደራ በብቃት ለመወጣት ያለሰዓት ገደብ የ24/7 የሥራ ባህልን በማጠናከር የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ዝግጅት መደረጉን አጽንኦት ሰጥተዋል።

በዚሁ የውይይት መድረክ ላይ ያለፉትን ዓመታት የሥራ አፈጻጸም ክፍተቶች በመሙላት፣ መልካም ተሞክሮዎችን በማጎልበት እና የአዲስ አበባን የብልጽግና ተምሳሌትነት ለማረጋገጥ የሚያስችል የጋራ መግባባት ላይ መደረሱ ተመላክቷል።
በመድረኩ ባለፉት የክረምት ወራት ከተያዙት የ90 ቀናት ዕቅድ ውስጥ የ60 ቀናትን አፈጻጸም መገምገም የተቻለ ሲሆን፤ የበዓላትን እና የክረምት ወቅትን ተከትሎ በኅብረተሰቡ ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ ጫናዎችን በሚቀንሱ እና የኑሮ ውድነትን በሚያቃልሉ ሥራዎች ላይ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ