AMN – ነሐሴ 26/2018 ዓ.ም
21ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የሕዝቦችን ትስስርና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን ይበልጥ በሚያጎላ መልኩ እንደሚከበር የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።
የ21ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል አስተባባሪ ዐቢይ ኮሚቴ በበዓሉ መሪ ዕቅድ ላይ የውይይት መድረክ እያካሔደ ይገኛል።
በውይይት መድረኩ የሁሉም ክልሎችና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች አፈ-ጉባዔዎች፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች፣ሚኒስትሮችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ የዘንድሮው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ኢትዮጵያ ያካሔደችው ስኬታማ ሀገራዊ ምርጫ እና ሀገራዊ ምክክር በውጤታማነት በተጠናቀቀበት ማግሥት መሆኑ ከወትሮው ለየት ያደርገዋል።
በዓሉ በሕዝቦች መካከል የሚደረጉ ባሕላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልውውጦችን በማስፋት ዘላቂ መከባበርና አብሮነትን ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
የበዓሉ ዝግጅት በየደረጃው ከሚገኙ ማኅበረሰቦች ጋር በመቀናጀት ሕዝባዊ መሠረቱን የጠበቀና ሕብረ-ብሔራዊ ውበቱን በሚገልጽ መልኩ እንዲከበር አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል።
21ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የሕዝቦችን ትስስርና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን ይበልጥ በሚያጎላ መልኩ እንደሚከበር ጠቅሰው፤ ለዚህም ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በዓሉ በክልሎች፣ በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች፣ በፌዴራል ተቋማት፣ ከሀገር ውጭ በኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ሲከበር ቆይቶ ኅዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ጅማ ከተማ ማጠቃለያው እንደሚሆን ኢዜአ ዘግቧል።