AMN- ነሐሴ 15/2018 ዓ.ም

የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ በሚመጡ የድርቅ፣ የጎርፍ እና የምግብ ዋስትና እክሎች እየተፈተነ ባለበት በዚህ ዘመን፣ ኢትዮጵያ ችግሩን በዝምታ ከመጠበቅ ይልቅ ተግባራዊና ዘላቂ መፍትሔዎችን በመቅረፅ ረገድ ግንባር ቀደም ሀገር ሆና ወጥታለች።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተጀመረውና በመላ ሀገሪቱ የተቀጣጠለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና ምድርን አረንጓዴ ለማልበስ የተካሄደ ታሪካዊ ዘመቻ ሆኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የምታደርገውን ጥረትና የያዘችውን ራዕይ ሲያስረዱ፣ “አረንጓዴ አሻራችን ለዛሬው ትውልድ የምግብ ዋስትና፣ ለነገው ትውልድ ደግሞ የህልውና መሰረት ነው” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።
እኛ የምንተክለው ችግኝ የዛሬዋን ብቻ ሳይሆን፣ የወደፊቷን ኢትዮጵያ እና አፍሪካን የአየር ንብረት ሚዛን የሚጠብቅ ነው በማለት የአረንጓዴ አሻራው እንቅስቃሴ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ፋይዳ ያለው መሆኑን አክለዋል።

ከ2011 እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ ከ48 ቢሊየን የሚልቁ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፣ ይህም ለአፈር ጥበቃ፣ ለደን ሽፋን ማደግና ለከርሰ-ምድር ውሃ መበልፀግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል።
የፍራፍሬና የአትክልት ችግኞችን በመትከል የተጀመረው ስራ ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ አስችሏል።

ሀገሪቱ የምታመርተውን የኤሌክትሪክ ኃይል ሙሉ በሙሉ ከውሃ፣ ከነፋስና ከፀሐይ በማመንጨት ዝቅተኛ የካርበን ልቀት ያለው ኢኮኖሚ ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሰራች ትገኛለች።
የካርበን ልቀትን ለመቀነስ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አጠቃቀም እንዲስፋፋ የማበረታቻ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ማድረጓም፣ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እያከናወነቻቸው ካሉ ዋና ዋና ተምሳሌታዊ ተግባራት መካከል ተጠቃሾች ናቸው።

ኢትዮጵያ ችግኞችን ለጎረቤት ሀገራት በማካፈልና በድንበር አካባቢዎች በመትከል የቀጣናዊ ትስስርና የጋራ ተፈጥሮ ጥበቃ ተምሳሌት ሆናለች።
እየተከናወነ ያለው የችግኝ ተከላና የአካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴ፣ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የምትሰጠውን ተግባራዊ ምላሽ የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ፣ ለቀጣዩ ትውልድ አረንጓዴና ለኑሮ ምቹ የሆነች ሀገር ለማስረከብ የተጣለ አስተማማኝ መሰረት ነው።
በታምራት ቢሻው