በበጀት ዓመቱ ሁሉም የመንግስት አገልግሎቶች ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል እንዲገቡ ይደረጋል

You are currently viewing በበጀት ዓመቱ ሁሉም የመንግስት አገልግሎቶች ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል እንዲገቡ ይደረጋል

AMN – ነሐሴ 26/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ በ2019 በጀት ዓመት ሁሉንም የመንግሥት የአገልግሎት ዘርፎች ወደ «መሶብ» የአንድ ማዕከል ዲጂታል አሰራር ለማስገባት አቅዶ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ ዶ/ር ጀማሉ ጀምበር የቢሮውን ዕቅድ አስመልክተው በሰጡት ገለጻ፤ ወደ መሶብ መግባት ያለባቸውን አገልግሎቶች በበጀት ዓመቱ ሙሉ ለሙሉ ለማካተት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

ስራውም ከከተማው የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ እንዲሁም ከመሶብ ማዕከል ጋር በጋራ በመሆን በየጊዜው እየተገመገመ እንደሚከናወን ገልጸዋል።

በዚህም በስራው የህዝብ አገልግሎት እርካታን እስከ 99 በመቶ ለማድረስ ታስቦ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በየወረዳዎች የሚስተዋሉ ያልተቀረፉ የአገልግሎት አሰጣጥ እና ምቹ የሥራ ቦታ ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት እንደሚሰራ የጠቆሙት ኃላፊው፤ በቀጣይ አምስት ዓመታት የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተደራሽነትን 66 በመቶ ለማድረስ መታቀዱንም ተናግረዋል።

እንደ ዶ/ር ጀማሉ ገለጻ፤ በበጀት ዓመቱ ተጨማሪ 20 ማዕከላትን ለመገንባት የታቀደ ሲሆን፤ የማዕከላት ማስፋፊያው የሚከናወነው በወረዳዎች መዋቅር ብቻ ሳይሆን የህዝብ አሰፋፈርን መሰረት ባደረገ መልኩ በክላስተር በማደራጀት ነው።

በቀጣይ አምስት ዓመታት በርካታ አገልግሎቶች በኦንላይን እንዲሰጡ ስለሚደረግ፤ የተደራሽነት ዕቅዱ ይህንን ዲጂታል አማራጭ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

ቢሮው በሥራ ዕድል ፈጠራ እና ተያያዥ የልማት ዕቅዶች ላይ ያተኮሩ ተግባራትን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አብራርተዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review