ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚዲያ ተቋማት ለሀገራዊ መግባባትና ለትርክት ግንባታ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ገለጹ

You are currently viewing ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚዲያ ተቋማት ለሀገራዊ መግባባትና ለትርክት ግንባታ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ገለጹ

AMN – ሚያዝያ 29/2018 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “የሚዲያ እመርታ ለትርክት ግንባታ” በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀ የምክክር መድረክ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፣ የሚዲያ ተቋማት ከዋልታ ረገጥነት ወጥተው ለሀገራዊ መግባባት በቁርጠኝነት እንዲሠሩ አስገንዝበዋል።

ባለፉት ዓመታት በሚዲያ ዘርፍና በተቋማት ግንባታ ላይ የተመዘገቡ ስኬቶች በቀረቡበት በዚህ መድረክ ላይ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚዲያውን ዘርፍ ወቅታዊ ሁኔታና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን በዝርዝር አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ እንዳመለከቱት፣ ባለፉት ስምንት ዓመታት የሚዲያ ምህዳሩን በዲሞክራሲያዊ አውድ ለመቃኘት የተወሰዱ እርምጃዎች ለሀገር ግንባታ የሚረዳ ጠንካራ መሠረት ጥለዋል።

ይህ በዘርፉ የተመዘገበው ውጤት ቀጣይነት እንዲኖረውም ሚዲያዎች ከጽንፈኝነትና ካልተገባ ወገንተኝነት በመውጣት በእውነት ላይ የተመሠረተ ትርክት የመገንባት ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የሚዲያዎችን ሙያዊ ብቃትና አሠራር በተመለከተም፣ ተቋማቱ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና በጥናት የታገዙ ጥልቅ ትንተናዎችን ማቅረብ እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

በተለይም ትኩረታቸው ተራ የርዕስ ሽያጭና የተመልካች ቁጥርን ብቻ ማሳደድ ሳይሆን ለሀገራዊ አጀንዳዎች ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባው አጽንኦት ሰጥተዋል።

የሚዲያ ተቋማት ተግባራቸው በግልጽ ዓላማ፣ በእይታ፣ በሙያዊ ብቃትና ለሕዝብ ቅርብ በመሆን ላይ ሊመሰረት እንደሚገባ ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሚዲያዎች ሚዛናዊነታቸውን ጠብቀው ለሀገር ብልጽግና መንገድ ጠራጊና ለችግሮች መፍትሔ አመላካች ሆነው እንዲቀጥሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review