ከንቲባ አዳነች አቤቤ 33ኛውን ከተማ አቀፍ የትምህርት ጉባኤ አስጀመሩ

You are currently viewing ከንቲባ አዳነች አቤቤ 33ኛውን ከተማ አቀፍ የትምህርት ጉባኤ አስጀመሩ

AMN- ነሐሴ 26/2018 ዓ.ም

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 33ኛውን ከተማ አቀፍ የትምህርት ጉባኤ “ብሩህ ነገን በዛሬ አዕምሮዎች” በሚል መሪ ቃል ዛሬ ማስጀመራቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገለጹ።

ይህ ጉባኤ በየዓመቱ የሚካሄደው የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ፣ ተደራሽነትን ለማስፋት፣ የመማር ማስተማር ሂደቱን ጤናማ እና ውጤታማ ለማድረግ መሆኑን ገለፀዋል፡፡

በተጨማሪም በዘርፉ የተሰሩትን ጠንካራ ስራዎች ልምድ የሚቀመርበት፣ የሚታረሙትንም ለይቶ በጋራ መፍትሄ በመስጠት እና የጋራ አቅጣጫ የሚይዝበት መሆኑ አመላክተዋል።

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በከተማ አስተዳደሩ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ የተማሪዎች ውጤት እየተሻሻለ መምጣቱን የገለጹት ከንቲባዋ፣ ዛሬ በከተማችን የትምህርት ውጤት ወደ 33 በመቶ መሻሻል ማሳየቱን ጠቁመዋል።

አሁንም ከፍ ያለ ውጤት እንደሚጠበቅ እና ገና ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅ አፅንኦት ሰጥተዋል።

መምህራን እና ባለድርሻ አካላት በእልህ ችግር የሚፈቱ፣ በሥነ ምግባር የታነፁ እና በእውቀት የታጠቁ ተማሪዎችን በብዛት ለመፍጠር መረባረብ እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ዋናውን ኢንቨስትመንት ትምህርት ላይ እናውል ብሎ ትልቁን በጀት ለትምህርት ዘርፍ እንዲሆን ማድረጉን ከንቲባዋ ጠቅሰው፣ በትውልድ ላይ ከመሰረቱ መስራት ወሳኝ በመሆኑ፣ የአዕምሮ እድገት ከጨቅላ ህፃንነት ወቅት በመሆኑ ከቀዳማይ ልጅነት ላይ እየተሰራ እንደሚገኝ አውስተዋል።

በዚህ አግባብ ከመሰረቱ ጀምሮ በመስራት በአንደኛ ደረጃ እንዲሁም በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ከፍተኛ ውጤት እና በዲሲፕሊን የታነፀ ትውልድ እንደሚጠበቅ ከንቲባዋ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review