AMN ሰኔ 29/ 2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ ትምህርት ቤቶች በ2018 የትምህርት ዘመን በተሰጠው የ6ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ መልቀቂያ ፈተና 98 በመቶ ከፍተኛ ውጤት ሆኖ መመዝገቡን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
በ2018 የትምህርት ዘመን በከተማ አስተዳደሩ 84 ሺህ 257 ተማሪዎች በ199 የፈተና ጣቢያዎች ፈተናው የተሰጠ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 82 ሺህ 137ቱ 50 እና ከዚያ በላይ ውጤት በማስመዝገብ ማለፋቸው ተገልጿል።
የቢሮው ሃላፊ ዶ/ር ዘላለም ሙላቱ በሰጡት መግለጫ ፈተናውን ካስፈተኑ 768 ትምህርት ቤቶች ውስጥ 548 ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን ሙሉ በሙሉ ማሳለፋቸውን ገልጸዋል።
98 ከመቶው ሁለት ተማሪዎች ማስመዝገባቸውን የገለፁት ቢሮ ሃላፊው 449 ተማሪዎች 95 እና ከዚያ በላይ፣ 5ሺህ 559 ተማሪዎች ደግሞ 90 እና ከዚያ በላይ እንዲሁም 82 ሺህ 137 ተማሪዎች ማለትም 97 ነጥብ 48 በመቶ 50 እና ከዚያ በላይ ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል።

በሁሉም ትምህርት ቤቶች የቀን ተማሪዎች ከተፈተኑት ውስጥ 97 ነጥብ 83 በመቶ ማለፋቸውን የገለጹት ዶ/ር ዘላለም በግል ከተፈተኑት ውስጥ ደግሞ 96 ነጥብ 66 በመቶ አልፈዋል ብለዋል።
ይህም የቀን የመንግስት 96 ነጥብ 80 በመቶ፣ የቀን የግል 99 ነጥብ 15 በመቶ፣ የመንግስት የማታ 91 ነጥብ 19 በመቶ፣ የግል የማታ 78 ነጥብ 92 በመቶ ማለፋቸውን አብራርተዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ ትምህርት ቤቶች በ2018 የትምህርት ዘመን የተሰጠው የ6ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና አጠቃላይ የማለፊያ ውጤት 50 በመቶ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በከተማ አስተዳደሩ በአጠቃላይ 84 ሺህ 257 ተማሪዎች በ199 የፈተና ጣቢያዎች ፈተናውን መውሰዳቸውን ገልጸው ከእነዚህ ውስጥ 82 ሺህ 137ቱ 50 እና ከዚያ በላይ አምጥተው ማለፋቸውን ገልጸዋል።

መደበኛ ተማሪዎች 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ፣ የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች 45 በመቶ ፣ የኦቲስቲክ፣ ዳውን ሲንድረምና ኢንተሌክቹዋል ዲሴቢሊቲ ያለባቸው ተማሪዎች 40 በመቶ የማለፊያ ውጤት እንዲሆን መወሰኑንም አብራርተዋል።
በ2018 የትምህርት ዘመን የ6ኛ ክፍል ተማሪዎችን ውጤት ከሌሎች ዓመታት የላቀ መሆኑን ያነሱት ሀላፊው የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ከመደበኛ ክፍለ-ጊዜ ውጭ የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት እንዲሁም ተማሪዎች በሒሳብና በእንግሊዘኛ ትምህርቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ልዩ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ መደረጉ ለተመዘገበው ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።