AMN- ነሐሴ 29/2018 ዓ.ም
የሕብረተሰብ ጤና ድምር ውጤቱ በተሰማራበት ዘርፍ ሁሉ ውጤታማ ተግባር የሚከውን እና ለሀገሩ ሁለንተናዊ ብልፅግና የሚተጋ አምራች ሕብረተሰብ መገንባት ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ኢትዮጵያን ላለፉት 100 ዓመታት ያገለገለውን፣ ታሪካዊ ወረት እና ዘመናዊ አቅምን ያጣመረውን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን የሥራ እንቅስቃሴ ተመልክተናል ብለዋል።
የሕብረተሰብን ጤና መጠበቅ ለዘላቂ ሀገራዊ ብልጽግና መሠረት ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ ተቋሙም በወረርሽኝ ልየታ፣ በበሽታ ክትትልና ምላሽ፣ በላብራቶሪ፣ በምርምር፣ በዲጂታላይዜሽን እና በጤና ስጋት ዝግጁነት የሀገሪቱን የጤና ሥርዓት በጥንካሬ እየደገፈ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡
በክልሎች የድንገተኛ ሕብረተሰብ ጤና አደጋ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከላትን ማቋቋሙና የሪፈራል ላብራቶሪዎችን ማስፋፋቱ የሀገሪቱን የጤና ዝግጁነት አቅም እያጠናከረ ያለ ወሳኝ ተግባር ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይም የአፍሪካ የሕብረተሰብ ጤና የልህቀት ማዕከል ለመሆን በከፍተኛ ትጋት እየሠራ ይገኛልም ነው ያሉት።
በተጨማሪም የዓለም የጤና ድርጅት የትብብር ማዕከል በመሆን ዓለም አቀፍ ሚናውን ለማጠናከር ብርቱ ጥረት እያደረገ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
የትላንትን ታሪክ ጠብቆ፣ ዛሬን በዘመናዊነት ዋጅቶ፣ ወደ ነገ የሚገሰግስ እንደዚህ ያለ ተቋምን መደገፍና ማጠናከር ለነገ የማንለው ተግባር ነው ብለዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፤ ኢንስቲትዩቱ የሀገርን ብልፅግና ለማፋጠን ወሳኝ አቅም በመሆኑ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡