የአረንጓዴ ዐሻራ ከተማዋን ለአየር ንብረት ተስማሚ እና ምቹ የቱሪዝም መዳረሻ አድርጓታል

You are currently viewing የአረንጓዴ ዐሻራ ከተማዋን ለአየር ንብረት ተስማሚ እና ምቹ የቱሪዝም መዳረሻ አድርጓታል

AMN- ጳጉሜን 1/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ በአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ ግብር እና በኮሪደር ልማት የተመዘገበው አስደናቂ እመርታ ከተማዋን ለአየር ንብረት ተስማሚ እና ምቹ የቱሪዝም መዳረሻ አድርጓታል፡፡

የደን ሽፋኗን በእጅጉ ያሳደገው እና የሕዝብን የባለቤትነት ስሜት ማዕከል ያደረገው ይህ የለውጥ ምዕራፍ ከተማዋ ለቱሪዝም እና ለምቹ መኖሪያነት ተመራጭ እያደረጋት ይገኛል።

ኢትዮጵያ በሰፊው የጀመረችው ሀገራዊ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከተሞችም ጭምር የራሳቸውን አሻራ እንዲያሳርፉ ሰፊ ዕድል ፈጥሯል።

ይህንን ሀገራዊ ራዕይ መነሻ በማድረግ አዲስ አበባ ባለፉት ዓመታት ያከናወነቻቸው የችግኝ ተከላ እና የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከተማዋ አስደናቂ እመርታ እንድታስመዘግብ አስችለዋታል፡፡

ከተማዋ የነበራትን አነስተኛ የደን ሽፋን ከማሳደግ ባለፈ የተራቆቱ ተራሮችን፣ የውሃ ማፋሰሻዎችን እና የወንዝ ዳርቻዎችን በስኬት መልሶ ማልማት ችላለች፡፡

በመዲናዋ በተከናወኑ ተከታታይ የችግኝ ተከላ እና የከተማ ጽዳት መርሐ ግብሮች ከተማዋ አሁን ወደ ተሻለ የኢኮሎጂ ደረጃ ተሸጋግራለች።

በተለይም በተራቆቱ ቦታዎች፣ በኮሪደር ልማት ጎዳናዎች እና መንገዶች ላይ በተከናወነ የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራ የከተማዋ የደን ሽፋን በአጭር ጊዜ ውስጥ አድጓል፡፡

ይህ እመርታ ከተማዋን ከብክለት አደጋ በመታደግ በምሥራቅ አፍሪካ አረንጓዴ እና ለአየር ንብረት ተስማሚ ከባቢ አላቸው ከሚባሉ ከተሞች አንዷ እንድትሆን አድርጓታል።

በከተማዋ ዙሪያ የሚገኙ እንደ እንጦጦ ያሉ ተራሮች ከነበሩበት ገጽታ ተላቀው በበርካታ ዛፎች ተሸፍነው አሁን ላይ ለነዋሪዎችና ለጎብኚዎች ታላቅ የቱሪዝም መዳረሻ መሆን ችለዋል።

ይህ የለውጥ ጉዞ የመንግሥት መዋቅር ብቻ ሳይሆን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች፣ የወጣቶች እና የባለሃብቶች የጋራ ትብብር ውጤት ነው፡፡

ችግኞችን ከመተከል ባለፈ የመንከባከብ እና የማሳደግ ጤናማ ባህል በከተማው ማኅበረሰብ ውስጥ እየጠነከረ መጥቷል።

ዘመናዊ እና ለአየር ንብረት የማይበገር ከተማ የመፍጠር አበረታች ርምጃም አሁን ላይ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review