AMN መስከረም 6/2019

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልዕክት በመላው ሀገራችን ለሚገኙ ተማሪዎቻችን አዲሱ የትምህርት ዘመን ስኬታማ እንዲሆን እንመኛለን ብለዋል።
ወጣቱ ትውልድ ለኢትዮጵያ ትልቁ ሀብቷ በመሆኑ የ2019 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ጅማሮን ተከትሎ፤ እያንዳንዱ ተማሪ ለላቀ እውቀት በትጋትና ጉጉት ትምህርቱን እንዲከታተል፣ ለጥሩ ውጤት በጽናት እንዲተጋ፣ እንዲሁም የሀገራችንን የወደፊት ዕድል መቅረጽ በሚያስችሉ ክህሎቶች እንዲገነባ አበረታታለሁ ብለዋል።

ዛሬ እየተገበርነው ያለው በርካታ የልማት ሥራዎች የነገን ትውልድ ታሳቢ ያደረጉ በመሆናቸው፣ የዚህ ቀጣይ ዕድል ተጠቃሚ እና ባለአደራ እንደመሆናችሁ መጠን፣ የኢትዮጵያን ታላቅ የስልጣኔ ታሪክ ወደፊት ለማስቀጠል የእናንተ ቁርጠኝነት መሠረት እንደሆነ ሙሉ እምነቴ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ብቁ እና በራሱ የሚተማመን ትውልድ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የመምህራኖቻችን ትጋትና መሰጠት መሰረታዊ ምሰሶ ነው።
ተማሪዎቻችንን ማነቃቃት፣ አቅማቸውን ማውጣት፣ እንዲሁም ነገ ተፎካካሪ ሆነው እንዲወጡ የሚያስችሏቸውን ዕውቀት፣ ክህሎትና እሴቶችን የማስታጠቅ አደራን ቀጥሉበት ስል በትህትና አሳስባለው ብለዋል።
በትምህርት ዘርፉ ውስጥ ለምትገኙ ባለድርሻ አካላት በሙሉ፤ ስኬታማ እና ፍሬያማ የትምህርት ዘመን እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መልዕክት አስተላልፈዋል።