ለትዉልድ ግንባታ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥታ በመስራት ላይ የምትገኘዉ የአፍሪካ መዲና

You are currently viewing ለትዉልድ ግንባታ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥታ በመስራት ላይ የምትገኘዉ የአፍሪካ መዲና

AMN – መስከረም 07/2019 ዓ.ም

የትውልድ ግንባታ ቤተሰብ፤ ማህበረሰብ እና ሃገር የሚፈልጉትን በሥነ ምግባር እና በእዉቀት የታነጸ ሀገር ወዳድ ዜጋን የማፍራት ሂደት ነዉ፡፡

የትውልድ ግንባታ ለሀገር ዕድገት እና ራዕይ መሳካት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለዉ ሲሆን የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ከፍታ በቀጣይነት የሚያስረክብ ኃይል ነዉ፡፡

በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ እና በዘመናዊ አስተሳሰብ የታነፀ ትውልድ ሀገሪቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንድትሆን ያስችላል።

ማህበራዊ እሴቶችን ያከብራል፤ ስለ ሃገሩ ሃላፊነት ይሰማዋል፤ ለሕግ እና ሥርዓት ከመገዛት አልፎ ሃሰተኛና የፈጠራ ወሬዎችንና ትርክቶችን ይጸየፋል፡፡

ትውልድን የመገንባት ሂደት የቤተሰብ፣ የትምህርት ተቋማት፤ የመንግሥት እና የሌሎች ባለድርሻ አካላት የጋራ ኃላፊነት ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ለዚሁ ሃገራዊ ራዕይ መሳካት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

በተለይ ከቅርብ አመታት ወዲህ በኮሪደር ልማትና በወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች በመዲናዋ የተገነቡት በርካታ የልማት ሥራዎች አዲሱን እና ቀጣዩን ትዉልድ ታሳቢ ያደረጉ ናቸዉ፡፡

ከተገነቡት መሰረተ ልማቶች መካከል የህጻናትና ወጣቶች የመጫወቻ ሥፍራዎች፤ የሕጻናት ማቆያዎች፤ የስፓርት ማዘዉተሪያና የመዝናኛ ሥፍራዎች፤ ቤተ መጽሃፍቶች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ዋንኞቹ ሲሆኑ በቀዳማይ ልጅነት መርሃ ግብርም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕጻናት የተለያዩ አገልግሎቶችን በማግኘት ላይ ይገኛሉ፡፡

ትምህርት ቤቶች ዋንኞቹ የትዉልድ መገንቢያ ማዕከላት እንደመሆናቸዉ መጠን የከተማ አስተዳደሩ ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ እስከ ሙያና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ድረስ ወጣቱን በሥነ ምግባርና በእዉቀት ለማነጽ የሚጠበቅበት ድጋፍ በሙሉ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

በምገባ እና በትምህርት ቁሳቁሶች ችግር ምክንያት ተማሪዎች የትምህርት እድል ማጣትና ከትምህርት ገበታዎች መቅረት የለባቸዉም በሚል ቁርጠኝነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎችን የተመጣጠነ ምግብ እየመገበ፤ የትምህርት ግብአቶችን እያቀረበ ማስተማሩም የከተማ አስተዳደሩ ለትዉልድ ግንባታ የሰጠዉን ትኩረት የሚያረጋግጥ ነዉ፡፡

የከተማ መስተዳድሩ “ትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ” በሚል ንቅናቄ ህብረተሰቡን በማሳተፍ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችንና የመማሪያ ክፍሎችን በመገንባትና በማስፋፋት፤ ደረጃቸውን የጠበቁ የመመገቢያ ቦታዎችን በማመቻቸት፣ ቤተ-መጻሕፍትና ቤተ-ሙከራዎችን በማዘመን ለትምህር ት ዘርፉ ተገቢዉን ድጋፍ በማድረግ ለትዉልድ ግንባታ በቢሊዮን የሚቆጠር በጀት ኢንቨስት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

የመዲናዋ ተማሪዎች የሂሳብ እና ሳይንስ ትምህርቶችን ጨምሮ በሌሎች የትምህርት አይነቶች የሚያስመዘግቡት ዉጤት በሃገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን ከሚያደርገዉ ብርቱ ጥረት ባሻገር በትምህርት ጥራት ላይ ትልቅ ፈተና ደቅኖ የነበረውን ኩረጃና የፈተና ስርቆት ከመሠረቱ ለማስወገድ የበይነ-መረብ ፈተና አሠራር ዘርግቶ ተጨባጭ ለዉጥ በማስመዝገብ ላይ ይገኛል፡፡

የትዉልድ ግንባታ ሂደት በመንግስት ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ጥረትና ድጋፍ የሚጠይቅ በመሆኑ በመዲናዋ የተጀመሩትን፤ በአህጉርና ዓለም አቀፍ ደረጃ እዉቅና የተቸራቸዉን መልካም ተሞክሮዎችንም በአዲሱ የትምህርት ዘመን አጠናክሮ ለመቀጠል ራዕይ ሰንቆ ወደ ስራ ገብቷል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review