የኢትዮጵያን ታላቅ የስልጣኔ ታሪክ ወደፊት ለማስቀጠል የአዲሱ ትዉልድ ቁርጠኝነት ትልቅ መሠረት ነዉ – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

AMN መስከረም 6/2019

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የ2019 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራ መጀመርን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት በመላው ሀገሪቱ ለሚገኙ ተማሪዎች አዲሱ የትምህርት ዘመን ስኬታማ እንዲሆን ተመኝተዋል።

‎ወጣቱ ትውልድ ለኢትዮጵያ ትልቁ ሀብቷ ነዉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ2019 ዓ.ም የትምህርት ዘመን እያንዳንዱ ተማሪ ለላቀ እውቀት በትጋትና ጉጉት ትምህርቱን መከታተልና ለጥሩ ውጤት በጽናት መትጋት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።

አዲሱ ትዉልድ የሀገሪቱን የወደፊት ዕድል መቅረጽ በሚያስችሉ ክህሎቶች እንዲገነባም አበረታተዋል።

‎በሃገሪቱ ዛሬ እየተተገበሩ የሚገኙት በርካታ የልማት ሥራዎች የነገን ትውልድ ታሳቢ ያደረጉ በመሆናቸው ትዉልዱ የዚህ ቀጣይ ዕድል ተጠቃሚ እና ባለአደራ መሆን ይኖርበታል።

የኢትዮጵያን ታላቅ የስልጣኔ ታሪክ ወደፊት ለማስቀጠል የአዲሱ ትዉልድ ቁርጠኝነት ትልቅ መሠረት መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላቸዉን እምነት ገልጸዋል።

‎ብቁ እና በራሱ የሚተማመን ትውልድ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የመምህራኖች ትጋትና መሰጠት መሰረታዊ ምሰሶ መሆኑንም አንስተዋል።

ተማሪዎቻችንን ማነቃቃት፣ አቅማቸውን ማውጣት፣ እንዲሁም ነገ ተፎካካሪ ሆነው እንዲወጡ የሚያስችሏቸውን ዕውቀት፣ ክህሎትና እሴቶችን የማስታጠቅ አደራን እንዲያስቀጥሉም በትህትና አሳስበዋል።

‎በትምህርት ዘርፉ ውስጥ የሚገኙ ባለድርሻ አካላትም ስኬታማ እና ፍሬያማ የትምህርት ዘመን እንዲሆን የበኩላቸዉን ሃላፊነት እንዲወጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መልዕክት አስተላልፈዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review