AMN – መስከረም 06/2019 ዓ.ም

አዲሱ የ2019 የትምህርት ዘመን መጀመርን ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በአዲስ መንፈስና በድምቀት ተከፍተዋል፡፡
የትምህርት ቤቶች መከፈትን ተከትሎም ተማሪዎች፣ ወላጆች እና መምህራን የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታና ተስፋ ለኤ አም ኤን አጋርተዋል፡፡
አዲሱ የትምህርት ዘመን መጀመሩ ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረላቸው የገለጹት ተማሪዎች፣ ከጓደኞቻቸውና ከአስተማሪዎቻቸው ጋር በመገናኘታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

በአካል ጉዳት ምክንያት ከቤት መውጣት ላልተቻለችና ትምህርት ቤት መከፈት ታላቅ ደስታ ለፈጠረባት ተማሪ ቢታኒያ ምስጋናው የዚህ ቀን መምጣት ልዩ ትርጉም ሰጥቶታል።
ተማሪ ቢታኒያ፤ ትምህርት ቤቴ ለእኔ በጣም ደስ የሚል ቦታ ነው፤ በጣም ነው የምወደው፤ በጣም ናፍቆኝ ነበር፤ እስከሚከፈትም በጣም ጓጉቼ ነበር” በማለት የናፍቆት ስሜቷን አጋርታለች።

ከዚህም በላይ የጎማ ወንበር (ዊልቸር) በመሰጠቷ በጣም ደስተኛ መሆኗን ተናግራለች።
ሌላኛዋ ተማሪ ረዴት ማሙሸትም ያለፈውን የትምህርት ዘመን ከጓደኞቿና አስተማሪዎቿ ጋር ያሳለፈችበትን ጊዜ አስታውሳ፣ አዲሱ የትምህርት ዘመን በመከፈቱ እና ወደ ትምህርት ቤት በመምጣቷ በጣም መደሰቷን ተናግራለች፡፡
ወላጆች በበኩላቸው መንግሥት ምንም ክፍያ ሳይጠይቅ በነፃ በማስተማሩና ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ልዩ ትኩረት በመስጠቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡

የተማሪ ቢታኒያ ወላጅ ወ/ሮ ስንታየሁ ደሳለኝ፤ ከዚህ ቀደም የዩኒፎርም፣ የደብተር እና የዊልቸር እጥረት አስቸግሯቸው እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ግን መንግሥት ደብተር፣ ቦርሳና ዩኒፎርም አሟልቶ በመስጠቱ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ማምጣት ብቻ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡
ሌላኛዋ የተማሪ ወላጅ ወ/ሮ ፋጡማ ኢብራሒም በበኩላቸው፤ የቁርስ፣ የምሳና የዩኒፎርም ጭንቀት እንደቀለለላቸው በመናገር ወላጆች በሰዓቱ ልጆቻቸውን አስገብተው በመቀበል ላይ ብቻ ማተኮራቸውን ገልጸዋል፡፡
መምህር ፋሲል ምስጋናው በሰጠው አስተያየት፣ መምህራን አሁን በአዲስ መንፈስ መነሳታቸውንና ለትምህርት ግብአት የሚያስፈልጉ ቅድመ ዝግጅቶችን ሁሉ ማድረጋቸውን ተናግሯል፡፡
መምህሩ ዓመታዊ እቅድ አቅዶና የሚያስፈልጉትን የክፍለ ጊዜ እቅዶች አዘጋጅቶ ትምህርቱ መጀመሩን ገልጾ፣ አስተማሪዎች ለማስተማር ያላቸው ሞራልና ተነሳሽነት በጣም የሚደነቅ መሆኑን አስገንዝቧል፡፡
በወርቅነህ አቢዮ