AMN-መስከረም 9/2019 ዓ.ም
በዴንማርክ ኮፐንሀገን የሚከናወነው የዓለም አትሌቲክስ የጎዳና ውድድር ዛሬ ይጀምራል።
ለሁለት ቀናት በሚከናወነው በዚህ ውድድር ላይ ዛሬ በመጀመሪያው ዕለት አትሌቶች በአራት ርቀቶች ይፎካከራሉ። በሁለቱም ፆታ የአንድ ማይል እና 5 ኪሎ ሜትር ውድድሮች ይከናወናሉ።
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሴቶች አንድ ማይል እና በ5 ኪሎ ሜትር በሁለቱም ፆታ ተሳታፊ ናቸው። በሴቶች አንድ ማይል ውድድር ፍሬወይኒ ሀይሉ እና ብርቄ ሀየሎም ይሳተፋሉ።
ፍሬወይኒ ውድድሩ አሁን በያዘው ቅርፅ ለመጀመሪያ ጊዜ በላቲቪያ ሪጋ ሲካሄድ በአንድ ማይል የነሐስ ሜዳልያ ማግኘት ችላ ነበር።
በሴቶች 5 ኪሎ ሜትር ጥሩ ብቃት ላይ የሚገኙት ልቅና አምባው እና አለሽኝ ባወቅ ኢትዮጵያን ይወክላሉ። ልቅና ወርልድ አትሌቲክስ ለመጀመሪያ ጊዜ ባካሄደው “አልቲሜት ቻምፒየንሺፕ” በ5000 ሜትር ተወዳድራ በድንቅ ብቃት ማሸነፏ ይታወሳል።
በወንዶች 5 ኪሎ ሜትር መዝገቡ ስሜ እና አዲሱ ይሁኔ ተሳታፊ ናቸው።
የትዉልድ ድምጽ የሆነዉ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዉድድሩን በቀጥታ ያሠራጫል።