AMN- መስከረም 9/2019 ዓ.ም
አምራች ኢንዱስትሪዎች ለአንድ ሃገር አጠቃላይ የውስጥ ምርት እድገት ያላቸው ድርሻ የላቀ ነው፡፡
በርካታ የዓለም ሃገራትም ለዘርፉ በሰጡት ልዩ ትኩረት የሃገራቸውን ሁለንተናዊ እድገት ከማረጋገጣቸውም በላይ የተሻለ ገቢ ያለውን ማህበረሰብ መፍጠር ችለዋል፡፡
ሃገራቱ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ጥገኛ መሆን ራስን እንዳለመቻል እና የሃገርን ሉዓላዊነት እንዳለማስበር ስለሚቆጥሩት ፈጠራን ባህል እስከማድረግ ደርሰዋል፡፡
ጀርመን፤ ቻይና፤ ሕንድ፤ ብራዚል፤ ደቡብ ኮሪያና ሌሎች ሃገራት የተለያየ የኢንዱስትሪ አካሄድን በመጠቀም በዕውቀትና በክህሎት የተገነባ አምራች የኢንዱስትሪ ዘርፍ መገንባት ችለዋል፡፡
በተለይ አሁን ካለንበት የዲጂታል ዘመን አንጻር የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከፍተኛ ለውጥ በማስተናገድ ላይ የሚገኝ ሲሆን ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ከምርት ሂደት ስርዓት ጋር በማጣመር ሃገራቱ ዘርፉን ይበልጥ ውጤታማ ማድረግ ችለዋል፡፡
ሃገራችን ኢትዮጵያም ግብርናን ማዕከል ያደረገ ጠንካራ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመገንባት በመስራት ላይ የምትገኝ ሲሆን ለኢንዱስትሪው አስቻይ ሁኔታዎችንና መሰረተ ልማቶችን በማጠናከር ላይ ትገኛለች፡፡
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዘርፉ የታጋረጠበትን ሁለንተናዊ ችግር መቅረፍ የቻለች ሲሆን በዚህም በርካታ ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት መሸጋገር ችለዋል፡፡
ዘርፉ የሚፈልገዉን የሰለጠነ የሰዉ ሃይል ከማፍራት ረገድም ለሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ለቴክኒክና ሞያ የትምህርት ዘርፎች ልዩ ትኩረት በመስጠት በተግባር የተደገፈ ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡

የግሉን ዘርፍ ጨምሮ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ድርጅቶች በኢንዱስትሪዉ ዘርፍ ዉስጥ ያላቸዉን ተሳትፎና ምርታማነት በማሳደግ የሥራ ዕድል ፈጣሪዎችና የኢኮኖሚ እድገት ሞተሮች ሆነዉ እንዲያገለግሉ እየተሰራ ነዉ፡፡
በጥሬ እቃዎች ላይ እሴት በመጨመር፤ የሚመረቱ ምርቶችን የጥራት ደረጃ በማሳደግ፤ ዓለማ አቀፋዊ ተወዳዳሪነታቸዉን በማሻሻል እና በተለያዩ የዓለም መድረኮች በማስተዋወቅ የማይበገር አምራች ኢንዱስትሪ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡
እስካሁን ድረስ በተሰራው ስራም የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም አጠቃቀም ከ51 በመቶ ወደ 69 ነጥብ 3 በመቶ ያደገ ሲሆን፤ የኤክስፖርት ገቢም በ2010 ዓ.ም ከነበረበት 308 ሚሊየን ዶላር በ2018 በጀት ዓመት ወደ 607 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር ማደግ ችሏል፡፡
የዘርፉ ድርሻ ከጠቅላላ ሀገር ውስጥ ምርት እድገት በ2010 በጀት ዓመት ከነበረበት 6 ነጥብ 2 በመቶ በ2018 ዓ.ም ወደ 6 ነጥብ 82 በመቶ ያደገ ሲሆን፤ የኢንዱስትሪው አማካኝ ዕድገትም በተጠቀሱት ዓመታት ውስጥ ከ5 ነጥብ 5 በመቶ ወደ 12 ነጥብ 7 በመቶ ከፍ ማለቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
የተገኙት ዉጤቶችም የኢትዮጵያን ማንሰራራት እዉን ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ፍሬአማ እየሆኑ መምጣታቸዉን የሚያመላክት ነዉ፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ