AMN – መስከረም 11/2019 ዓ.ም

ስፖርት ከአካል ብቃትና ከመዝናናት አልፎ የከተሞችን ኢኮኖሚ፣ ገጽታ እና የቱሪዝም ፍሰት የሚቀይር ትልቅ ኢንዱስትሪ ነው።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት በየዓመቱ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚስበው የስፖርት ቱሪዝም የብዙ ታዋቂ ከተሞች ዋነኛ የገቢ ምንጭ ሆኗል።
ለመሆኑ ስማቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ በወርቃማ ፊደላት ያስጻፉ ከተሞች ምን ሠርተው ተሳካላቸው?
ባርሴሎና ከ1992ቱ ኦሎምፒክ በፊት የወንዞች ዳርቻና የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎቿ ብዙም ሳቢ አልነበሩም።
በኦሎምፒኩ ምክንያት የወንዞች ዳርቻዎቿን በማስዋብ፣ አዳዲስ ስታዲየሞችንና የህዝብ መዝናኛዎችን በመገንባት ከተማዋን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መቀየር ተችሏል።
ዛሬ ላይ ከካምፕ ኑ ስታዲየም እና ከስፖርት ዘርፍ ብቻ በየዓመቱ ቢሊየን ዩሮዎችን ታገኛለች።
የስፖርት፣ የባህልና የንግድ ማዕከል የሆነችው ሌላኛዋ የዓለም አቀፍ ስፖርቶች መናኸሪያ ለንደን ነች።
እንደ ዊምብልደን (ቴኒስ)፣ የለንደን ማራቶን እና የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን በማስተናገድ ቀዳሚ ናት።
ግዙፍና ዘመናዊ ስታዲየሞችን ከመገንባት ባሻገር ከተማዋን ለመላው ዓለም የስፖርት አፍቃሪዎች ምቹና የተሳሰረች የትራንስፖርት ስርዓት ያላት በማድረጓ ስፖርትን ከባህልና ከንግድ ጋር አጣጥማለች፤ በዚህም ረብጣ ገንዘብ ወደ ካዝናዋ ታስገባለች።
እንዲሁም የስፖርት ዋና ከተማ ሜልቦርን በዓለም ላይ “የስፖርት ከተማ” በመባል ትታወቃለች።
ሚስጥሩ ደግሞ ሁሉንም ዋና ዋና የስፖርት ማዕከላት (የአውስትራሊያን ኦፕን ቴኒስ፣ የፎርሙላ 1 ግራንድ ፕሪ እና የክሪኬት ሜዳዎች) በአንድ የተሰባሰበ የስፖርት ማዕከል ውስጥ አደራጅታ መገንባቷ እና ዓመቱን ሙሉ የማይቋረጡ ውድድሮችን ማዘጋጀቷ ነው።
ለስፖርት ቱሪዝም የተከፈተው አዲስ ምዕራፍ የጀግኖች አትሌቶች መፍለቂያ የሆነችው አዲስ አበባ፣ የስፖርት ታሪኳን ወደ ስፖርት ቱሪዝም የመቀየር ትልቅ አቅም እያደራጀች ትገኛለች።
በቅርብ ጊዜያት ለስፖርት የተሰጠው ልዩ ትኩረት ከተማዋን የስፖርት ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ትልቅ መሠረት ጥሏል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተከናወኑ የኮሪደር ልማቶች የተፈጠሩ የእግረኛ መንገዶችና የብስክሌት መስመሮች እንዲሁም የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች የከተማ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን የሚያበረታታ አዲስ ባህል እያዳበሩ ይገኛሉ።
የወዳጅነት፣ የእንጦጦ እና የአድዋ መታሰቢያ አደባባይ ፓርኮች ተፈጥሮን ከስፖርት ጋር በማጣመር ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ጎብኚዎች ልዩ ትኩረት የሚስቡ ሆነዋል።
በእንጦጦ እና በሌሎች የከተማዋ ክፍሎች የሚገኙ የስፖርት ማዕከላት ስፖርታዊ ውድድር ፍላጎትና መነሳሳትን ከፍ አድርገውታል።
አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት እና የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ እንደመሆኗ መጠን፣ ትላልቅ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮችን፣ የሩጫ መድረኮችንና ማራቶኖችን ለማስተናገድ የሚያስችሉ መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት ላይ ትገኛለች።
በያለው ጌታነህ