AMN – መስከረም 11/2019 ዓ.ም

ፖለቲካ አንድ ማህበረሰብ የሚመራበት፣ ስልጣን የሚያዝበት፣ ሃብት የሚተዳደርበት እና የህዝብ ጉዳዮች የሚወሰኑበት ስርዓት፣ አስተዳደርና ጥበብ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ፖለቲካ የአንድን ማህበረሰብ የጋራ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያገለግል ከመሆኑም በላይ የዜጎችን ሰላም፣ ደህንነት፣ ነፃነት እና የጋራ ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች የሚሰሩበት ስርዓትም ነው፡፡
የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ያላቸውን ፍላጎቶች እና እምነቶች በሰላማዊ መንገድ በማስታረቅ የጋራ መግባባት ላይ የሚደረስበትም ሂደት ነው፡፡
ፖለቲካ እነዚህንና መሰል በጎ ጽንሰ-ሀሳቦችን የያዘ፣ በሀገር አስተዳደርና በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ውስጥ የላቀ ድርሻ ያለው ስርዓት ሲሆን በርካታ ሀገራትም ይህንኑ አስተዳደር በመጠቀም ጠንካራ ሀገረ-መንግስት እስከመገንባት ደርሰዋል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ፍላጎቶች እና እምነቶች የሚያስታርቀው፣ ሰላማዊና የጋራ መግባባትን የሚፈጥረው ፖለቲካዊ አካሄድ ግጭትን ማዕከል ባደረገው የፖለቲካ ስልት በመሸጋገር ላይ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በተለይ ለስልጣን የሚፎካከሩ አንዳንድ የፖለቲካ ሃይሎች ማህበራዊ ውጥረቶችን፣ ልዩነቶችን እና አለመግባባቶችን በመጠቀም መንግስትን ለመክሰስና የራሳቸውን አጀንዳ ለማራመድ ይጥራሉ፡፡

ኅብረተሰቡን በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ እና በተለያዩ መንገዶች በመከፋፈል፣ የመንግስትን ሃይል በማዳከም እና አንዱን ከሌላው ጋር በማጣላት ራሳቸውን የበላይና የመፍትሄው አካል ለማድረግ ይሰራሉ፡፡
በሌሎች ቡድኖች ላይ ስጋት እና ጥላቻ የሚፈጥሩ ትርክቶችን በመንዛት ሕዝቡ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል በፍርሃት እና በንዴት እንዲነሳሳ ያደርጋሉ፡፡
ግጭትን ለፖለቲካ ዓላማ የሚጠቀሙት እነዚህ ሃይሎች ግጭትና አለመረጋጋትን በመፍጠር አለበለዚያም አለመረጋጋትን በማባባስ ሕዝቡ ለአደጋ እንዲጋለጥ ያደርጋሉ፤ ከዚያ በኋላም ራሳቸውን የህዝቡ ዋና መሪ፣ ነጻ አውጪ እና ተሟጋች አድርገው ይሾማሉ።
ይህንን የፖለቲካ ስልት የሚጠቀሙ ኃይሎች ፓለቲካዊ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ንጹሐን ዜጎችን ለሞት፣ ለአካል ጉዳት እና ከቀያቸው መፈናቀል ይዳርጋሉ፤ መሠረተ ልማቶችን ያወድማሉ፤ ንግድና ኢንቨስትመንት ይቆማል፣ ድህነት እንዲባባስ ያደርጋሉ፡፡
ግጭትን ለጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም ማዋል በረጅም ጊዜ የተገነባን ሀገር የማፍረስ አቅም ያለው ሲሆን የሀገር ህልውናን አደጋ ውስጥ የመጣል እና ማህበራዊ መስተጋብርን ሙሉ በሙሉ የመሸርሸር እድል እንዳለውም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በመጠፋፋት ላይ የተመሰረተውን ይህንን የፖለቲካ አካሄድ ለመከላከል የህዝቦችን ወንድማማችነት፣ አብሮነትና አንድነት ማጠናከር እንደሚገባ ምሁራን ይመክራሉ፡፡
ጥላቻን የሚያነሳሱ፣ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ እና ግጭትን ለፖለቲካ ንግድ የሚጠቀሙ አካላት በህግ አግባብ መጠየቅ ይኖርባቸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከበስተጀርባ ሆነው ግጭትን የሚቀሰቅሱ የፖለቲካ ሰዎች እና ቡድኖች ያለምንም የፖለቲካ ጥገኝነት በሕግ ሊጠየቁ ይገባል፡፡
በዘር ወይም በሃይማኖት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ እሳቤ የሀገርን እና የህዝቦችን ወንድማማችነት፣ አብሮነትና አንድነት እንዳይሸረሽር በህግ አግባብ ክትትል ሊደረግበት ይገባል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች እና መሪዎቻቸው ከጥልና ከልዩነት ይልቅ ሰላማዊ ውይይትን እና አብሮነትን የሚያስቀድሙ የስነ-ምግባር መርሆዎችን መከተል እንደሚገባቸው ነው ምሁራን የሚመክሩት፡፡
መገናኛ ብዙሃን በበኩላቸው በህዝቦች መካከል ልዩነትን እና መቃቃርን ሊፈጥሩ ከሚችሉ የጥላቻ ንግግሮችና ሀሰተኛ ትርክቶች ከማሰራጨት እንዲታቀቡ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ኅብረተሰቡ በተለይም ወጣቱ ትውልድ የፖለቲካ አሻጥር ሰለባ እንዳይሆን በባህል፣ በትምህርት እና በማኅበራዊ መድረኮች የሰላም እና የጋራ መግባባት እሴቶችን ማጠናከር እንደሚገባው ነው የዘርፉ ምሁራን የሚያሳስቡት፡፡
ግጭትን ለጊዜያዊ ጥቅም ማዋል ማህበራዊ መሠረትን የሚያናጋ እና ሀገርን ለከፍተኛ አደጋ የሚዳርግ በመሆኑ፣ መንግሥት፣ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ሲቪክ ማህበራት እና አጠቃላይ ኅብረተሰቡ በጋራ መቆምና አደጋውን መከላከል ይኖርባቸዋል፡
በወንድማገኝ አሰፋ