አዲስ አበባ ለአፍሪካ ሕፃናት የብልጽግና ተምሳሌት እየሆነች ነው

AMN – ጥቅምት 4/2019 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መዲናዋን በአፍሪካ ሕፃናትን ለማሳደግ እና ለመንከባከብ ምርጥ ከተማ ለማድረግ ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነት በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል።

ለዚህ ታላቅ ዓላማ ስኬት አስተዳደሩ በሕፃናት የመጀመሪያ እድገትና እንክብካቤ ላይ ያተኮሩ ተግባራትን ዋና የልማት አጀንዳ በማድረግ ሰፊ እንቅስቃሴዎችን እያካሄደ ነው።

የከተማ አስተዳደሩ የሕፃናትን ደህንነት፣ የጤና አጠባበቅ፣ የቀደመ ትምህርት እና ሁለንተናዊ የወደፊት ሕይወት ለማሻሻል ያቀዳቸውን ስትራቴጂዎች ወደ ተጨባጭ ተግባር እየቀየረ ይገኛል፡፡

በከተማዋ ደረጃቸውን የጠበቁና ዘመናዊ ቁሳቁሶች የተሟሉላቸው የሕፃናት ማቆያና እንክብካቤ ማዕከላት በስፋት እየተገነቡ ይገኛሉ።

የከተማ አስተዳደሩ በሕፃናት ላይ እያከናወነ የሚገኘው ይህ በጎ ተግባር ለአፍሪካ ከተሞች ተምሳሌት መሆን መጀመሩን ከንቲባ አዳነች አበቤ ገልጸዋል።

አዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀዳማይ ልጅነት ዓለም አቀፍ ጉባኤን ከወራት በፊት ያስተናገደች ሲሆን፣ ዛሬም ለሁለተኛ ጊዜ የአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎች አመራር ኢኒሼቲቭ የ2026 የአመራሮች ፎረም ተሳታፊዎችን ተቀብላ እያስተናገደች እንደምትገኝ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታውቀዋል።

የአዲስ አበባ የልማት ተሞክሮ ለሌሎች የአፍሪካና የዓለም ከተሞች ጠቃሚ ትምህርቶችን እያበረከተና አዳዲስ የልማት ዕድሎችን እያመላከተ መሆኑን ከንቲባዋ አብራርተዋል።

በተለይም አዲስ አበባን በአፍሪካ ሕፃናትን ለማሳደግ ምርጥ ከተማ ለማድረግ ባለው ቁርጠኝነት፣ በሕፃናት እድገት ላይ ያተኮሩ ተግባራት ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በዚህም መሠረት መዲናዋ ለመጀመሪያ ጊዜ ባካሄደችው የቀዳማይ ልጅነት ዓለም አቀፍ ጉባኤ ለመታደም ከተለያዩ ሀገራት የመጡ እንግዶች፣ አዲስ አበባ እያከናወነች ያለችው የልማት ተግባር ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።

በተጨማሪም የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሺም ሼቲማ እና ልዑካቸው አዲስ አበባ በተግባር የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ያስመዘገበቻቸውን ውጤቶች፣ ልምዶችና ተሞክሮዎች በሀገራቸው ለሚተገብሩት መሰል ተግባር ከፍተኛ አርአያ እንደሆናቸው መግለጻቸው አይዘነጋም።

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review