አዲስ አበባ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያደገችበትና የተለወጠችበት ምስጢር ምን ይሆን?

You are currently viewing አዲስ አበባ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያደገችበትና የተለወጠችበት ምስጢር ምን ይሆን?

AMN- መስከረም 16/2019 ዓ.ም

አዲስ አበባ ከስልሳ ወይም ከሰባ ዓመታት በፊት ጠባብና ከከተማነት ይልቅ ገጠርነት የከተጫናት ከተማ ነበረች፡፡

ይህ ሁኔታ በመካከለኛው የከተማዋ ክፍል እስከ ቅርብ ዘመን እምብዛም አልተቀየረም፡፡

የከተማዋ አብዛኛው ክፍል ኮሸኮሽ አካባቢ ተብሎ ሊጠራ የሚችል አካባቢ ነበር፡፡ እነዚህ መንደሮች የከተማዋን መሠረተ ልማት አዉታራት ለማስተካከልና ለመገንባት ገዳቢ ሆነዉ ቆይተዋል፡፡

አዲስ አበባን ሕይወት አልባ ካደረጓት ምክንያቶች አንዱ መንገድና በመንገድ ዙሪያ ያሉ ችግሮች ሲሆኑ ፤ መዲናዋ አሁን ላይ ዘመናዊ የተሽከርካሪ መንገዶች ፤ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶች ፤ ፋውንቴኖች ፤ የማረፊያ ስራዎች ፤ የመኪና ማቆሚያዎች ፤ የመዝናኛና መጫወቻ ስፍራዎች ፤ የንግድና የመኖሪያ መንደሮች እንዲሁም የልዩ ልዩ መሰረተ ልማቶች ባለቤት ሆናለች፡፡

ማስተካከልን ፤ ማዘመንን ፤ ማሳመርንና ማመቻቸትን መርህ አድርጎ በመዲናዋ የተከናወነው አጠቃላይ የልማት ስራ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ አበባ አድርጓታል፡፡

መልክና ውበት አልባ ሆኖ ፤ ተደበላልቆ የነበረው የህንጻዎች ቀለም እርስ በርሱ የተጣጣመ እንዲሆን የተደረገ ሲሆን ማስተካከያው ከአይን ውበት አልፎ የአየር ንብረት ለውጥን ማስተካከል በሚያስችል ደረጃ አረንጓዴ ሆኖ እንዲያምር ተደርጓል፡፡

የቆሻሻ ወጋገድ ሥርዓቱ እጅግ ከመዘመኑም በላይ ፤ የእሳት አደጋን በቀላሉ መቆጣጠርና ውሃ መቅዳት የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶች በየአካባቢው ተገንብተዋል፡፡ የውሃ ፤ የኤሌክትሪክ ፤ የፍሳሽ ፤ የቴሌ መስመሮች ለጥገና ምቹ ሆነዋል፡፡

አዲስ አበባ ለሁሉም ነዋሪዎቿ በተለይም ለአካል ጉዳተኞች፤ ለአረጋዊያን፤ ለህጻናትና ወጣቶች ምቹ ሆና ተገንብታለች፡፡

አብዛኞቹ መንገዶቿ ነዋሪው በቀላሉ መንቀሳቀስና አእምሮውን ማዝናናት እንዲችል ሆነው የተገነቡ ሲሆን የመኖሪያ ሰፈሮችም ለኑሮ ተስማሚና ማራኪ ሆነዋል፡፡

አዲስ አበባ አሁን ላይ ቀንና ሌሊት ለሚሰሩ የተለያዩ የንግድ ስራዎች ምቹ ከመሆኗም በላይ ለቱሪዝም ፣ ለፈጠራ ስራዎች ፣ ለደጂታል ቴክኖሎጂ እና መሰል ዘርፎችም ምቹ ከተማ ሆናለች፡፡

አዲስ አበባ የአፍሪካ እና የተቀረው አለም መነጋገሪያ የሆኑትን እነዚህንና መሰል ፈጣን ለውጦች ያስመዘገበችው በጥቂት አመታት ውስጥ ሲሆን የዚህ ስኬት ዋንኛው ምስጢር ህብረተሰቡን አስተባብሮ 24/7 የመስራት አዲሱ የስራ ባህል ነው፡፡

አዲስ አበባ ላይ አሁን ህብረተሰቡን አስተባብሮ ቀን በጸሃይ ብርሃን ፣ ሌሊት በመብራት ያለማቋረጥ መስራት ባህል እየሆነ መጥቷል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ሁሉም ዜጎች ባህልና ገንዘብ ሊያደርጉት የሚገባ ትልቅ ተሞክሮ ሆኗል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ አበባ ለማድረግ የወጠነው ራዕይ ፤ በ24/7 አዲሱ የሥራ ባህል ፣ በህብረተሰብ ተሳትፎ ፤ በአመራሩና ሰራተኛው ቁርጠኝነት ፣ በኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች ፣ በሰፊ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችና የመልሶ ማልማት ስራዎች እውን ሆኗል፡፡

አዲስ አበባ ካሉባት ችግር ተላቅቃ የመጪው ዘመን ከተማ እንድትሆን ባለፉት ጥቂት አመታት የተሰሩት ስራዎች መዲናዋ በአፍሪካና በአለም አቀፍ ደረጃ ልምድ የሚቀመርባት ከተማ ከመሆን አልፋ የተለያዩ እውቅናዎችን እስከማግኘት ደርሳለች፡፡

መዲናዋ አሁን ላይ ለነዋሪዎቿና ለቱሪስቶች ፤ ለፈጠራና ለኢንተርፕሪነርሺፕ እንዲሁም ለንግድና ለግብይት ምቹ ወደ መሆን ተሸጋግራለች፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review