ደማቁ የመስቀል በዓል አከባበር – በመርካቶ የበጎነት መንደር

AMN- መስከረም 17/2019 ዓ.ም

ለዓመታት በበርካታ የተወሳሰቡ ችግሮች ተተብትቦና ለሰው ልጅ ክብር በማይመጥን ሁኔታ ውስጥ ቆይቶ የነበረው የቀድሞው የመርካቶ “ቅጠል ተራ” አዲስ ታሪክ ተጽፎበታል።

የአዲስ አበባ ከተማ በአጭር ጊዜ ውስጥ ገንብቶ ባጠናቀቀው የአሁኑ «የመርካቶ የበጎነት መንደር» ዘመናዊ መኖሪያ ስፍራ ነዋሪዎች የዘንድሮን የመስቀል በዓል በደስታ አክብረዋል።

የቀድሞው “ቅጠል ተራ” ለኑሮ እጅግ አስቸጋሪ፣ የተጨናነቀ ከመሆኑም በላይ በእሳት አደጋ የነዋሪዎችን ሕይወት ጭምር ሲቀጥፍ የኖረ ነበር።

ሆኖም ከተማ አስተዳደሩ በ11 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በ4 ወራት ውስጥ የገነባቸው G+8 የሆኑ ዘጠኝ ብሎኮች የነዋሪዎችን ህይወት ቀይረዋል።

በአጠቃላይ 960 ቤቶችን ያካተተው ይህ የመርካቶ የበጎነት መንደር፤ ሰፊ የስራ እድልን የሚፈጥሩ 371 የንግድ ሱቆች፣ የህጻናት መጫወቻና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ የመኪና ማቆሚያ፣ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ ማድረጊያ እንዲሁም የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገድ ተሟልቶለታል።

ኤ ኤም ኤን በመርካቶ የበጎነት መንደር ተገኝቶ ነዋሪዎች የመጀመሪያውን የመስቀል በዓል በአዲሱ ቤታቸው እንዴት እያከበሩ እንደሆነ ተመልክቷል።

በዚህም ቀደም ሲል በአስቸጋሪ መኖሪያ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ እናቶችና ወጣቶች ዛሬ የዘመናዊ ቤት ባለቤት በመሆናቸው በዓሉን በደስታ አክብረዋል።

ነዋሪዎቹ እንደገለጹት፤ የዘመናዊ ቤት ባለቤት መሆናቸው የከተማ አስተዳደሩ የልማት አቅጣጫ ዋና አላማ የዜጎችን ክብር ማስጠበቅና የኑሮ ደረጃን ማሻሻል መሆኑን በተግባር ያረጋገጠ ነው።

በከተማ አስተዳደሩ “ታሪክ ተሰርቷል” የሚሉት ነዋሪዎቹ፤ እንዲህ አይነት ሰው ተኮር ልማቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተለያዩ ጊዜያት እንዳስታወቁት፤ ከተማ አስተዳደሩ የነዋሪዎችን ኑሮ ለማሻሻልና ለማዘመን በወሰደው የአመራር ቁርጠኝነት እንዲሁም በ24/7 የስራ ባህል መሰል የተወሳሰቡ ችግሮች ያሉባቸውን አካባቢዎች ወደ ምቹ የመኖሪያ መንደሮች የመቀየር ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል።

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review