በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ውስጥ የሚገኘውን የበአሉ ማክበሪያ ስፍራን ጨምሮ አካባቢውን ጽዱ፣ ውብና ማራኪ ለማድረግ የጽዳት ዘመቻ ተካሂዷል።
በፅዳት ዘመቻው ወቅት የተገኙት የአዲስ አበባ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ጀማሉ ጀንበር ባደረጉት ንግግር ኢሬቻ በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሀብት ብቻ ስይሆን የአንድነት፣ የፍቅር፣ የሰላም እና የእርቅ ማዕከል የሆነ በዓል በመሆኑም በዐሉን ለማክበር ከመላው ዓለም እና ከሀገሪቱ ሁሉም ማዕዘን እና የከተማዋ ነዋሪዎች በዓሉን ለማክበር እንደሚታደሙ ገልፀዋል ።

አክለውም ለዚህ ክብረ በዓል የሚመጡ እንግዶችን መቀበል፣ መንከባከብና በዓሉ በሰላም ተጠናቆ እንግዶችን በሰላም መሸኘት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በዚህ የጽዳት ዘመቻ ዶክተር ጀማሉን ጨምሮ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ዶክተር ማሾ ኦላና፣ የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ተፈራ ሞላ፣ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ መዓዛ መንግሥቱ፣ በክፍለ ከተማው የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ አበራ፣ እንዲሁም የፊንፊኔ ሕብረት ሰብሳቢ አባ ገዳ ቦኪ ገመቹ እና ሌሎች አባገዳዎች ጨምሮ በየደረጃው ያሉ አመራሮች፣ የጽዳት አምባሳደሮች፣ ታዋቂ ሰዎች እና ነዋሪዎች ተገኝተዋል።