AMN – ኅዳር 7/2019 ዓ.ም
የመደመር መንግስት በአምስት ዓመታት ውስጥ የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ የገባውን ቃል፣ ቀንና ሌሊት በቅንጅት በመስራት በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል።
ዜጎች በመኖሪያ ቤት እጥረት ምክንያት የሚገጥማቸውን ፈተናና ሥጋት ለመቅረፍ፤ ደረጃቸውን ጠብቀው በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርቡ መኖሪያ ቤቶችን ለማመቻቸት በትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡
በሀገሪቱ የቤቶች ልማትን በከፍተኛ ፍጥነት ተደራሽ ለማድረግም የኮንስትራክሽን ግብዓት አቅርቦትን ማሻሻል ወሳኝ እንደሆነ መንግስት ያምናል።
ለዚህ ይረዳ ዘንድ እንደ ብረት፣ መስታወት እና ሴራሚክ ያሉ መሠረታዊ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።
ዜጎች ቤቶችን በቀላሉ መግዛት እንዲችሉም ከባንኮች ጋር በመተባበር የተመቻቹ የሞርጌጅ ፋይናንስ እና የክፍያ ማዕቀፎች፣ ለብዙዎች የቤት ባለቤትነት ዕውን መሆን ከፍተኛ ፋይዳ አላቸው።
የመደመር መንግስት በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት የተገባውን ቃል ለማሳካት ሰፊ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
ሰሞኑን ይፋ እንዳደረገውም፣ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በ21 ሳይቶች 100 ሺህ ቤቶች በግንባታ ላይ ናቸው።
ከእነዚህ ውስጥ 50 ሺህ ቤቶች በከተማው በጀት ሲሸፈኑ፣ ቀሪዎቹ 50 ሺህ ቤቶች ደግሞ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት እንዲሁም በቤት ልማት ማኅበራት እየተገነቡ ይገኛሉ።
አብዛኛዎቹ እነዚህ ፕሮጀክቶች ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ለተጠቃሚዎች የሚበቁ መሆናቸው፣ የመንግሥትና የግል አጋርነት ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ የሚያሳይ ሕያው ምስክር ነው።
ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቱሉ ዲምቱ የሚገኙ 33 ብሎኮችን እና በአዲስ ከተማ መርካቶ ቅጠል ተራ የሚገኙ 9 ብሎኮችን በመጎብኘት የግንባታ ሂደታቸውን ተመልክተዋል፤ ፕሮጀክቶቹም በጥሩ የአፈጻጸም ሂደት ላይ መሆናቸውን ገምግመዋል።
በመርካቶ ቅጠል ተራ የተገነቡት ዘጠኝ የመኖሪያ ቤት ሕንፃዎች ከተራ የግንባታ ሥራ በላይ የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ የሚቀይሩ፣ የቤተሰቦችን ተስፋ የሚያድሱና ማኅበራዊ ፍትህን በተግባር የሚያረጋግጡ ማሳያዎች ሆነዋል።
የመደመር መንግስት አሁን ላይ ዋናውና ታላቁ ግብ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ሕይወት መቀየር፣ የዜጎችን የቤት ጫና ማቃለል ነው።
በበረከት ጌታቸው