የሆረ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል የብሔር ብሔረሰቦች የአንድነት እና የፍቅር መድረክ ነው- የተለያዩ ብሔር ታዳሚዎች

You are currently viewing የሆረ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል የብሔር ብሔረሰቦች የአንድነት እና የፍቅር መድረክ ነው- የተለያዩ ብሔር ታዳሚዎች

AMN- መስከረም 23/2019 ዓ.ም

በሆረ ፊንፊኔ በአዲስ አበባ በታላቅ ድምቀት ተከብሮ በዋለው የኢሬቻ በዓል ላይ ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመጡ ታዳሚዎች በዓሉ የአንድነት፣ የፍቅርና የምስጋና መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።

ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉ የበዓሉ ታዳሚዎች በሰጡት አስተያየት፣ የኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ህዝብ ባህልና እሴት ከመሆን አልፎ፣ የኢትዮጵያዊያንን አንድነትና ህብረት የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።

ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከከምባታ ዞን የመጡ ታዳሚዎች፣ የኢሬቻ በዓል በአንድነት፣ በአብሮነትና በፍቅር መኖር መሆኑን ገልጸው፣ የቀደሙ አባቶቻችን ያስተላለፉልንን ባህልና እሴት አብሮ ማክበር ትልቅ እርካታን ይሰጣል ብለዋል።

አክለውም አዲስ አበባም የብሔር ብሔረሰቦች ከተማና የአፍሪካ መዲና በመሆኗ፣ አሁን ላይ የተዘረጉ የኮሪደር እና የተለያዩ ልማቶች ከተማዋን እንደ ስሟ ውብ አድርገዋታል ብለዋል።

በተመሳሳይም ከወላይታ እና ሀላባ ዞኖች የመጡ ታዳሚዎች በበኩላቸው፣ የበዓሉ ድባብ፣ ማህበረሰቡ ያሳየው አቀባበልና መስተንግዶ እጅግ ማራኪና ደስ የሚል እንደነበር ገልጸዋል።

በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወነው መሠረተ ልማት ለበዓሉ ድምቀት ተጨማሪ ውበት መስጠቱንና ለታዳሚው የተለየ ስሜት መፍጠሩንም አብራርተዋል።

በዓሉ ባህላዊ ትውፊቱን በጠበቀ መንገድ በአንድነትና በፍቅር የተከበረ ሲሆን፣ ታዳሚዎችም በየዓመቱ በአንድነት ተሰብስበው አብሮነታቸውን የሚያጠናክሩበት ታላቅ የምስጋና በዓል መሆኑን ገልጸዋል።

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review