AMN መስከረም 24/ 2019 ዓ.ም
የኮማንዶ እና አየር ወለድ ሠራዊት ለሰው ልጆች ያለውን ጥልቅ አክብሮት በተግባር ያስመሰከረ እና በበርካታ የውጊያ አውዶችም የዓላማ ጽናቱን ያረጋገጠ ነው።
ባለቀዩ መለዮ በየዘመናቱ የተደቀኑትን ፈተናዎች እና ተግዳሮቶች በድል በማለፍ ሀገር የጣለችበትን ልዩ ግዳጆች በላቀ ብቃት የመወጣት አቅሙን በተግባር አሳይቷል።
ጀግና እና ጀግንነት በሚፈተኑበት የጦር ግንባር ውስጥም በከፍተኛ የሥልጠና ጥራት ያዳበረውን አቅም በጥምር ጦር የውጊያ ስልት በመጠቀም የማይሽር የታሪክ ገድል ይጽፋል።
የዚህ ሠራዊት ጀግንነት ከጽንፈኝነት፣ ከዘር፣ ከሃይማኖት እና ከማንነት ልዩነት የጸዳ ነው። ሕዝብን በቅንነት ለማገልገል ባለው ጽኑ የሙያ ሥነ ምግባር ላይ የተቃኘ በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኩራት ለመሆን በቅቷል።
ይልቁንም የወቅቱን ዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ ነባራዊ ሁኔታ አስቀድሞ በመገምገም ራሱን ከሁኔታዎች በፊት ዝግጁ የማድረግ የዳበረ ተቋማዊ ባህል ነው ጠንካራ ያደረገው።
ከተልዕኮዎቹ እና ተሞክሮዎች ትምህርት በመውሰድ የራሱን ጥንካሬ እና ክፍተት በየጊዜው በመለየት እንዲሁም የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውጤቶችን በሥልጠና ሥርዓቱ ውስጥ በማካተት ብቃቱን በቀጣይነት እያሳደገ ይገኛል።

ዘመናዊ ሠራዊት መገንባት መሣሪያን በማዘመን ብቻ ሳይወሰን የሰው ኃይልን፣ የሥልጠና ሥርዓትን፣ የመረጃ አቅምን እና የጥበብ አመራርን በጥምረት ማጎልበትን ይጠይቃል።
በዚህም መሠረት ኮማንዶው ያለፈውን የጀግንነት ትሩፋት ከዛሬው ዘመናዊ ወታደራዊ ሳይንስ ጋር በማጣመር ለነገው ደኅንነት የተሟላ ዝግጁነት ያለው አቅም ፈጥሯል።
የዚህ ድል አድራጊ ሠራዊት ዋነኛ የኃይል ምንጭ ከሕዝብ ጋር ያለው ጥልቅ ትስስር ነው። ሕዝብን የተልዕኮው ማዕከል አድርጎ መሥራቱ እና የኢትዮጵያ ጠላቶች የሚያሰራጩትን የሐሰት ትርክት በተግባር ማክሸፍ መቻሉ ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር ያለውን መተማመን ይበልጥ አጠናክሮታል።
የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ጠባቂነት ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር ታላቅ አደራ ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ ኮማንዶ እና አየር ወለድ ሠራዊት ከሌሎቹ አጋር ክፍሎች ጋር የትናንት ጀግንነቱን መሠረት አድርጎ የዛሬን ዘመናዊነት አቅም ፈጥሮ፣ እንዲሁም የነገን ዝግጁነት አረጋግጦ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የሕዝብን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ማስጠበቁን ቀጥሏል። – የሃገር መከላከያ ኦንላይን ሚዲያ