የጡት ካንሰር ምልክቶችና ሕክምና

AMN- ጥቅምት 2/2019 ዓ.ም

የጡት ካንሰር በሴቶች ላይ ከሚከሰቱ የካንሰር ዓይነቶች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው።

በሽታው በጊዜ ከታወቀ እና አስፈላጊው የሕክምና ክትትል ከተደረገለት እስከ 95 በመቶ የመዳን ዕድል አለው።

የጡት ካንሰር የሚከሰተው በጡት ውስጥ የሚገኙ ሕዋሳት ከተፈጥሯዊ የሰውነት ቁጥጥር ውጪ በሆነ መንገድ ከመጠን በላይ ሲራቡ እና ሲያድጉ ነው።

እነዚህ ሕዋሳት ቅርጻቸውን እና ባህሪያቸውን በመቀየር በጡት ውስጥ እብጠት የሚፈጥሩ ሲሆን፣ በጊዜ ካልታከሙ በደም ዝውውር አማካኝነት ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ሊሰራጩ ይችላሉ።

የጡት ካንሰር በዓለም አቀፍ ደረጃ 99 በመቶ በሴቶች ላይ የሚከሰት ቢሆንም፣ 1 በመቶ ያህሉ ግን በወንዶች ላይ ይከሰታል።

በኢትዮጵያ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በወንዶች ላይ ያለው ሥርጭት እስከ 5 በመቶ ይደርሳል።

ለጡት ካንሰር በሽታ ቀጥተኛ መንስኤው እስከ አሁን ባይታወቅም፣ በእድሜ መግፋት፣ በቅርብ ዘመድ ውስጥ የጡት ካንሰር ታሪክ መኖር፣ የወር አበባ ቀድሞ መምጣት ወይም ዘግይቶ መቋረጥ፣ የአልኮል መጠጥ ማብዛት፣ ሲጋራ ማጨስ፣ ቅባት የበዛባቸው ምግቦችን ማዘውተር እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ እንደ አጋላጭ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ።

በጡት ወይም በብብት ሥር የሚወጣ እብጠት፣ የጡት ጫፍ ወደ ውስጥ መሰርጎድ ወይም ከጡት ጫፍ ያልተለመደ ፈሳሽ መውጣት፣ በጡት ቆዳ ላይ የሚታይ የቆዳ ቀለም ወይም ቅርጽ ለውጥ፣ የቆዳ መሸብሸብ ወይም ቁስለት የበሽታው ዋና ዋና ምልክቶች መሆቸውን የሕክምና ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

በሽታውን ለመለየት የመጀመሪያው የሕክምና እርምጃ አካላዊ ምርመራ ማድረግ ነው፡፡

በተጨማሪም የአልትራሳውንድ እና የማሞግራፊ ምርመራዎች፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም የሕብረ ሕዋሳት ናሙና ምርመራ ይደረጋል።

በሽታው ከተከሰተ በኋላ እብጠቱን ወይም ሙሉ የጡትን ክፍል በቀዶ ህክምና ማስወገድ፣ እንዲሁም በኪሞቴራፒ እና በሬዲዮቴራፒ የካንሰር ሕዋሳትን ለማጥፋት የሚያስችሉ ሕክምናዎች ይሰጣሉ።

ይህንን አደገኛ በሽታ ለመከላከልም በየዓመቱ ጥቅምት ወር ዓለም አቀፍ የጡት ካንሰር ግንዛቤ ማስጨበጫ ወር ሆኗል፡፡

ይህንን የግንዛቤ ማሻሻያ ወርን ምክንያት በማድረግም በየአካባቢው የጡት ካንሰር የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራዎች ይደረጋሉ።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review