AMN – ጥቅምት 2/2019 ዓ.ም

በትግራይ ክልል የሚገኙ የዓዲ ጉዶም ከተማ ነዋሪዎች የፌደራል መንግሥት ወደ አካባቢያቸው መግባቱን የሚደግፍና የህገወጡን የህወሃት ቡድን ድርጊት የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል።
ሰልፈኞቹ በአካባቢው ሰላም በመስፈኑ የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታና የተስፋ ብርሃን ገልጸዋል።
በሰልፉ ላይ የተሳተፉ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት፣ ቀደም ሲል በቡድኑ ይካሄድ በነበረው በግዴታ የታጣቂዎች ምልመላ፣ የህፃናትና ወጣቶች አፈና እንዲሁም በነበረው የጦርነት ሁኔታ ተስፋ ቆርጠው ይኖሩ እንደነበር አስታውሰዋል።

ነገር ግን የፌደራል መንግሥት አካባቢውን ከተቆጣጠረ በኋላ የተፈጠረው ሰላምና መረጋጋት አዲስ የተስፋ ብርሃን ፈንጥቆልናል ብለዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ አክለው እንደገለጹት፣ ቡድኑ ህፃናትን እና ወጣቶችን በግዴታ እየመለመለ ወደ ጦር ግንባር ይወስድ እንደነበርና ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ተመልሰው እንዳልመጡ አስታውሰዋል፡፡

የመጡትም ቢሆኑ በደረሰባቸው ከባድ የአካል ጉዳት ምክንያት አሰቃቂ ህይወት ለመኖር መገደዳቸውን በቁጭት ገልጸዋል።
ከጦርነት ይልቅ ሰላም ሲሰፍን ልጆቻችንን አሳድገን ለቁም ነገር ማብቃት እና ሰላማዊ ህይወት መኖር እንፈልጋለን ሲሉም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
ቀደም ሲል በነበረው አስተዳደር በየአካባቢው ምንም አይነት የልማት ስራ እንዳልተሰራ፤ የመብራት፣ የውሃ እና የመንገድ መሰረተ ልማቶች አሁንም ከባድ ችግር እንዳለባቸው ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል።
አክለውም እኛ ኢትዮጵያውያን ነን፤ ወደፊት ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወንድምና እህቶቻችን ጋር በመሆን አካባቢያችንን ለማልማትና እድገትን ለማምጣት በጋራ ለመስራት ዝግጁ እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡
በሰልፉ ላይ ነዋሪዎቹ “ድል ለትግራይ ህዝብ!” እና “ድል ለፌደራል መንግሥት!” የሚሉ መልዕልቶችን በማስተጋባት ደስታቸውንና ድጋፋቸውን ገልጸዋል።
በአስማረ መኮንን