AMN- ጥቅምት 2/2019 ዓ.ም

የአድዋ ጀግኖች የዉጭ ወራሪ ሃይሎችን በጋራ መክተዉ ኢትዮጵያ የነጻነት ቀንዲል እንድትባል ያደረጉት በጽኑ ሃገራዊ ፍቅርና ወኔ ነዉ፡፡
ከተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችና ሃይማኖቶች እንዲሁም ከመላ ሃገሪቱ የተዉጣጡት እነዚያ የአድዋ ጀግኖች በአንዲት ሰንደቅ አላማ በጋራ ተሰባስበዉና መክረዉ የሃገራቸዉን አንድነትና ሉዓላዊነት አስከብረዋል፡፡
የአድዋ ድል እና ሠንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ታሪክ ሲሆኑ በልዩነቶች መካከል በጋራ መቆም እንዴት እንደሚቻል በተግባር አረጋግጧል፡፡
የአድዋን ጀግኖች የአርበኝነትና የጀግንነት መንፈስ የተጋሩት ኢትዮጵያዊያንም በተለያዩ ጊዜያት ሃገሪቱ የጋጠሟትን
ፈተናዎችና ትንኮሳዎችን በጽናት በመታገል ለባንዲራቸዉ ያላቸዉን ክብር አስመስክረዋል፡፡

ከሃገሬና ከባንዲራዬ በፊት እኔ ልሰዋ፤ ከሃገሬና ከህዝቤ የሚበልጥብኝ የለም፤ ነጻነት ክብር ነዉ፤ ባርነት ዉርደት ነዉ በሚል ጽኑ አቋም በርካታ የኢትዮጵያ ጀግኖች መራራ ጽዋን ተጎንጭተዋል፡፡
በተለይ ጀግናዉ የሃገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች ጸጥታ አካላት ለሰንደቅ አላማ ያላቸዉ ክብር የተለየ ሲሆን እስከ ህይወት መስዋዕትነት የሚደርስ ዉለታን ለሃገራቸዉ ይከፍላሉ፡፡
የሃገራቸዉን ሰንደቅ አላማ ተንበርክከዉ በመቀባበል፤ በባንዲራቸዉ ፊት በጀግንነት ቆመዉ የሃገራቸዉን ብሄራዊ የህዝብ መዝሙር በመዘመር እና ሰንደቅ አላማቸዉን ከፍ በማድረግ፤ በግዳጅ ቦታዎች ጭምር ሰንደቅ አላማቸዉን አንግበዉ በመታገል፤ ድል ባደረጉባቸዉ ቦታዎችም በደስታ እንባ ታጥበዉ ባንዲራቸዉን ከፍ አድርገዉ በማዉለብለብ ለሃገራቸዉ ያላቸዉን ፍቅርና ክብር ይገልጻሉ፡፡
በዚህያዉ ልክ የሃገርን ክብርና ባንዲራን አሳልፈዉ የሚሸጡ የዉስጥ ባንዳዎችና የዉጭ ጠላቶችን አምርረዉ ይታገላሉ፡፡
በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ሃገርና ባንዲራን መክዳት ከህግ፤ከሞራል፤ ከባህልና ከሃይማኖት አንጻር የተወገዘ ሲሆን በእንደዚህ አይነት ተግባር ላይ መሳተፍም ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል፡፡
ከዚህ በተቃራኒዉ በርካታ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ለሃገር ትልቅ ዉለታን በመዋል፤ የሃገርን ስም በማስጠራት፤ ባንዲራን ከፍ በማድረግ፤ እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብለዉ በድፍረት በመናገር አርበኝነታቸዉን፤ ጀግንነታቸዉን እና ለሃገራቸዉ ክብር ያላቸዉን ስሜት ይገልጻሉ፡፡
በርካታ የኢትዮጵያ ልጆች ዛሬም በሃገር ዉስጥ እና በዉጭ ሃገራት ጭምር በየተሰማሩበት የስራ መስክ የሃገራቸዉን መልካም ገጽታና ክብር የሚያጎሉ ተግባራትን በመፈጸም ታሪክ የማይዘነጋዉን ዉለታ ለሃገራቸዉ በመክፈል ላይ ይገኛሉ፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ