የሳይበር ደኅንነት የሀገር ደኅንነት ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

AMN-ጥቅምት 2/2019 ዓ.ም

የሳይበር ደኅንነት የሀገር ደኅንነት ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ዛሬ የ7ኛውን ሀገር አቀፍ የሳይበር ደኅንነት ወር “ንቁ ዜጋ፤ ደኅንነቱ ለተጠበቀ ሀገር!” በሚል መሪ ሐሳብ በይፋ አስጀምረናል ብለዋል፡፡

በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ያሳካናቸው የኢንተርኔት ተጠቃሚነት መስፋፋት፣ የቴሌኮም ዘርፉ ለውድድር መከፈት፣ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶች መስፋፋትና የመንግሥት አገልግሎቶችን በዲጂታል መንገድ የማቅረብ ርምጃዎች ለዲጂታል ሽግግር መሠረት እንደጣሉ አንስተዋል፡፡

ይህንን ወደ ቀጣይ ምዕራፍ በማሸጋገር፣ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ራዕያችንን እውን ለማድረግና የቴክኖሎጂ ዕድገት የሀገራዊ ብልጽግናችን ወሳኝ ዐቅም እንዲሆን በሁሉም መስክ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የሀገሪቱን የሳይበር ምኅዳር ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ በማድረግ፣ ለሀገራዊ ልማት፣ ለዲጂታል 2030 ስትራቴጂ ስኬት እና ለላቀ ሀገራዊ ብልጽግና የሚያደርገውን የ24/7 ጥረት ዕውቅና መስጠት ያስፈልጋልም ነው ያሉት፡፡

የዲጂታል ምኅዳራችንን ከሳይበር ሥጋቶች መጠበቅ የሀገራችንን የዲጂታል ሉዓላዊነት፣ የዜጎችን ደኅንነትና የልማት ጉዟችንን የማስጠበቅ ጉዳይ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

አክለውም፤ የዲጂታል ምኅዳራችንን የሚጠብቅ፣ የሀገራችንን ደኅንነት የሚያጠናክርና የዲጂታል ጉዟችንን የሚያረጋግጥ ንቁና ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ መገንባት ከሁላችንም ይጠበቃል ብለዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review