ትናንት – ዛሬ እና ነገ እየታረቁ ነዉ!

AMN- ጥቅምት 3/2019 ዓ.ም

የዓድዋ ጀግኖች በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ እና በጾታ ሳይለያዩ በጋራ ዘምተው የሀገራቸውን ነጻነትና ሉዓላዊነት በማስከበር ጠንካራ የጋራ ትርክትን ገንብተው አልፈዋል።

ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ የነበሩት ፖለቲካዊ ሥርዓቶች ህዝቡን ማስተሳሰር የሚችል የጋራ አጀንዳ መፍጠር ባለመቻላቸው ሀገሪቱ የተለያዩ ስብራቶችን ለማስተናገድ ተገዳ ነበር።

መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፣ የነበሩት መንግስታዊ ሥርዓቶች በማንነት ላይ የሚያተኩሩ፣ ለልዩነት ቦታ የሚሰጡ እና አለመግባባት የሰፈነባቸው በመሆናቸው ሀገሪቱ ለግጭትና ለፖለቲካዊ አለመረጋጋት ተዳርጋ ቆይታለች።

ይህም የሀገሪቱ ፖለቲካ ሁለት ጽንፍ በያዙ ማንነቶች እና በአክራሪ ብሔርተኝነት እንዲወጠር ምክንያት ሆኗል።

በዚህም በሐሳብ ገበያው እኩል ቀርቦ ከመወዳደር ይልቅ በዋልታ ረገጥ ትርክትና ሽኩቻ ሲናጥ መቆየቱ፣ አማራጭ ሀሳብ አለመኖሩ፣ ልዩነትን በአግባቡ ከማቻቻል ይልቅ መከፋፈል፣ ሚዛንን ከመጠበቅ ይልቅ ያልተገባ ሽኩቻን መፍጠር፣ በአነስተኛና በአንጻራዊ የጥቅም ፉክክር ውስጥ መዘፈቅ ከነበሩት ሀገራዊ ስብራቶች መካከል ዋናኞቹ ነበሩ።

ዋልታ ረገጥ ትርክቶችን ሊያስታርቅ የሚችል ሶስተኛ ሃሳብ እና አቀራራቢ ታሪክ መፍጠር አለመቻሉ፣ ህዝቡ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እኩል ተሳትፎ እንዳይኖረው እና የነገውን እጣ ፈንታ በጋራ እንዳይወስን እንቅፋት ሆኖበት ቆይቷል።

የለዉጡ መንግስት ለረጅም ዘመናት ስር ሰደው ለነበሩት የልዩነት፣ የሽኩቻና የመጠፋፋት መንስኤ ለሆኑ የፖለቲካ እሳቤዎች፣ ሦስተኛውን አማራጭ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል።

ይህ አዲስ አማራጭ ለዘላቂ ሀገራዊ ሰላምና ልማት የጋራ ሀገራዊ ትርክትን መገንባት ያስፈልጋል ብሎ የሚያምን ሲሆን፣ እሳቤውም ከአክራሪ ማንነቶች በመውጣት በሀሳብ ልዕልና ማመን ላይ የተመሠረተ ነው።

በዚህም አግላይ የፖለቲካ ማንነቶች፣ ዋልታ ረገጥ እሳቤዎች እና የመጠፋፋት አዝማሚያዎች እየታከሙ መጥተዋል።

ነፃነትን፣ እኩልነትን፣ ወንድማማችነትና እህትማማችነትን መሰረት ያደረገው እሳቤ በመጠናከር ላይ ይገኛል።

የትናንትን ብቻ ሳይሆን የዛሬ አብሮነትን እና የነገ የጋራ እጣ ፈንታን የሚያመላክት የጋራ አጀንዳ እየተገነባ መጥቷል።

ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የሚያጠናክር፣ ህዝብን አስተባብሮ ወደ አንድ የብልጽግና ዓላማ የሚመራ እና ብሔራዊ መግባባትን የሚፈጥር ምቹ መደላድል ተፈጥሯል።

የፖለቲካ ኃይሎችን ጨምሮ መላው ህዝብ ከአነስተኛ ጥቅም ተላቆ ለአንድ ሀገራዊ ግብ በጋራ መቆም ጀምሯል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የዚሁ ብሔራዊ ትርክት ውጤት ሲሆን፣ በህዝቦች መካከል ያለውን አንድነት ይበልጥ ከማጠናከሩም በላይ እንደ ሀገር በጋራ የመበልጸግ ርዕይን ፈጥሯል።

በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ እንደ “ዳግማዊ ዓድዋ” የሚታየው ይህ ፕሮጀክት፣ ኢትዮጵያውያን ዛሬም ልዩነቶቻቸውን አክብረውና አንድነታቸውን ጠብቀው አዲስ ታሪክ መስራት እንደሚችሉ በተግባር ያረጋገጠ ነው።

ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት ስትጠቀምበት የነበረውን የባህር በር ያጣችው በዚሁ የመከፋፈልና የመጠፋፋት ፖለቲካ በሀገሪቱ ውስጥ በነገሰበት ወቅት ነበር።

ዛሬ ላይ ግን ሁሉንም ዜጎች ማግባባት የሚችል የጋራ ትርክት በመገንባቱ፣ መላው የሀገሪቱ ዜጎች ያለምንም ልዩነት የግብጽ ተላላኪ የሆኑትን ህገ-ወጡን የህወሃት ቡድን እና ሻዕቢያን በጋራ በመታገል ላይ ይገኛሉ።

በአክራሪ ማንነትና በተለያዩ ፖለቲካዊ ስብራቶች ምክንያት የተለያየ ጽንፍ ይዘዉ የነበሩ የፖለቲካ ሃይሎች፤ ታጣቂዎች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም ዙሪያ በጋራ መቆም እና መፋለም ጀምረዋል፡፡

መረጃዎች እንደሚያመላክቱትም፣ በርካታ የጽንፈኛው ቡድን ታጣቂዎች “በግብጽ ሴራ እናት ሀገራችንን አናፈርስም” በማለት ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት እጅ መስጠት ጀምረዋል።

አንዳንድ የሻዕቢያ ታጣቂዎችም ይህንኑ የግብጽን ሀገር የማፍረስ ተልዕኮ በመቃወም ለሰራዊቱ እጃቸውን እየሰጡ ይገኛሉ።

በትግራይ ክልል ሰሞኑን በተካሄዱ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፎች ላይ ህዝቡ በኢትዮጵያዊነቱ ከማንም ጋር የማይደራደር፣ እንዲሁም ህገ-ወጡን የህወሃት ቡድን፣ ጽምዶን እና ሻዕቢያን አምርሮ የሚታገል መሆኑ ተረጋገጧል።

ኢትዮጵያ በህገ-ወጥ መንገድ ያጣችውን የባህር በር ማግኘቷ ከጂኦግራፊ እስረኝነት ነጻ እንደሚያወጣት፣ ሉዓላዊነቷን እንደሚያስከብር እና የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ ወደ ተሻለ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግር የጋራ መግባባት መፈጠሩ ለኢትዮጵያውያን ተጨማሪ ታላቅ ድል ሆኖ በመመዝገብ ላይ ይገኛል።

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review