አዲሱ ምዕራፍ የኢትዮጵያን ሀብቶች ወደ ተጨባጭ ልማት፣ የቴክኖሎጂ እድገት እና ወደ ጋራ ብልጽግና መለወጥ ላይ ያተኩራል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር)

You are currently viewing አዲሱ ምዕራፍ የኢትዮጵያን ሀብቶች ወደ ተጨባጭ ልማት፣ የቴክኖሎጂ እድገት እና ወደ ጋራ ብልጽግና መለወጥ ላይ ያተኩራል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር)

AMN – ጥቅምት 11/2019 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽንን መጎብኘታቸውን በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ይህ ተቋም ለኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የልማት ርዕይ ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።

ኢትዮጵያ እጅግ ከፍተኛ በሆነ እምቅ አቅሟ እና በተትረፈረፈ ተፈጥሯዊ ሀብቷ ለረጅም ጊዜ ትታወቃለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ አዲሱ ምዕራፍ ደግሞ እነዚህን ሀብቶች ወደ ተጨባጭ ልማት፣ የቴክኖሎጂ እድገት እና ወደ ጋራ ብልጽግና መለወጥ ላይ ያተኩራል ብለዋል።

አስተማማኝና ዘላቂ የኃይል አቅርቦት ለኢንዱስትሪ፣ ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለዲጂታል መሠረተ ልማትና ለአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ማዕከላዊ ሚና እንዳለውም ጠቅሰዋል።

የኒውክሊየር ቴክኖሎጂ ደግሞ የኃይል ዋስትናን በማጠናከር እየገሰገሰ ያለውን ፍላጎት ለማሟላት ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ፤ ከኃይል ምርት ባለፈ በጤና፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአካባቢ ጥበቃ ዘርፎች ለሀገራዊ ልማትና ለቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ መሠረታዊ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) በመልዕክታቸው እንደገለጹት ፣ የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን ለብሔራዊ የኒውክሊየር ኃይል ፕሮግራም አስፈላጊ የሆኑትን ተቋማዊ እና ቴክኒካዊ መሠረቶች በመጣል ይህንን ርዕይ ለማሳካት ስትራቴጂካዊ ሚና አለው።

ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት፣ ሳይንሳዊ ምርምርን ማስፋፋት እና የተቋሙን ዕውቀት ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ወሳኝ ተግባራት ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ ይህም ብሔራዊ አቅምንና ልዩ ሙያዊ ብቃትን በማዳበር የኒውክሊየር ኃይል ልማት ሰላማዊ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ አስተማማኝ እና ዘላቂ በሆነ መንገድ በኃላፊነት ስሜት እንዲከወን ያደርጋል ብለዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review