የኢትዮጵያን ታላቅነት እና የአካባቢዉን ወቅታዊ ሁኔታ ያገናዘበ የመከላከያ ሃይል እየተገነባ ነዉ- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing የኢትዮጵያን ታላቅነት እና የአካባቢዉን ወቅታዊ ሁኔታ ያገናዘበ የመከላከያ ሃይል እየተገነባ ነዉ- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN መስከረም 26/2019

የኢትዮጵያን ታላቅነት፣ የዓለም እና የአካባቢያችን ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም የወደፊቱን የዓለም አካሄድ ያገናዘበ የመከላከያ ሃይል እንዲኖረን እንሰራለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢፌዴሪ 7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የምክር ቤቱ መመሥረቻ 1ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ዘመናዊ፣ ፈጣሪ፣ ሁሌም ዝግጁ፣ ብቁና ንቁ፣ በየአውዶቹ የመሰማራት አቅምና ቁመና ያለው መከላከያ እየተገነባ መሆኑን ተናግረዋል።

ችግሮች ሳይፈጠሩ አስቀድሞ ማወቅና መግታት፣ ከመጡም መከላከል፣ ከባሰም እንደ አባቶቹ እንደ ልማዱ ማሸነፍ የሚችል ሃይል ሆኖ መገንባቱን ይቀጥላል ነዉ ያሉት።

ሁለንተናዊ ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠች፣ ህብረ-ብሄራዊ አንድነቷ የጸና፣ ምርታማነትን ባህል ለማድረግ የምትተጋ፣ መሪና ፈር ቀዳጅ የሆነች አይበገሬ ኢትዮጵያን የመገንባት ታሪካዊ ዕድል ከፊታችን አለ ብለዋል።

በቀጣዮቹ ዓመታት የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ዓለም አቀፍ ተጽዕኖዋን በሚያሳደግ መልኩ እንደሚቃኝም አንስተዋል። ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ግንኙነት ብሔራዊ ጥቅሟን መሰረት አድረጋ ትሠራለች።

ጎረቤት ሀገራት በተፈጥሮ የተገናኙ ወዳጆች መሆናቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከሁሉም ጋር በሰላም፣ በጋራ ጥቅም እና በትብብር የመስራት መርሃችን እንገፋበታለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ስልጣኔ ያለ ባህር በር እውን ሊሆን አይችልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ የመግቢያ በር እንዲኖራት ተግተው እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review