AMN- ጥቅምት 16/2019 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ወንዞች ከብክለትና ከተፈጥሮ መራቆት ወደ ንጹህ፣ ማራኪና ለነዋሪዎች ምቹ የከተማ ሕይወት ማዕከላትነት እየተሸጋገሩ ነው።
ይህ የወንዞች ትንሳኤ ብቻ ሳይሆን፣ ከተማችንን ለቱሪዝም ምቹ የሚያደርጋት፣ የዲፕሎማቲክ ማዕከልነቷን የሚያጎለብትና አዲስ ገጽታ የሚያሳይ ታላቅ ለውጥ ነው።
ከቀጨኔ፣ በአምባሳደር፣ ጊዮን፣ ኢሬቻ እስከ ባምቢስ የሚዘልቀው እና ትናንት የተመረቀው የወንዝ ዳርቻ ልማት፤ የወንዞችን ዳርቻ ወደ ውብ የመዝናኛ፣ የማኅበራዊ ትስስርና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ማዕከልነት የሚቀይር የመደመር መንግሥት የከተማ ልማት ቱሩፋት ነው።
ይህ ልማት ለነዋሪዎች ከውበት በላይ የሆነ ትርጉም አለው። ለቤተሰቦች የመዝናኛና የእረፍት ስፍራ፣ ለወጣቶች የፈጠራና የሥራ ዕድል፣ ለአካባቢው ነጋዴዎች የኢኮኖሚ ተሳትፎ ዕድል፣ ለከተማዋም የተፈጥሮ ሀብትን የሚጠብቅና የአካባቢ ጥራትን የሚያሻሽል ዘላቂ ልማት መሠረት ይሆናል።
አዲስ አበባ ዛሬ የወንዞቿን ዳርቻ ብቻ አታለማም፤ የነዋሪዎቿን የኑሮ ጥራት፣ የከተማዋን ውበትና የወደፊት ዕድሏን እየገነባች ነው።

ከተፈጥሮ ጋር የተስማማ፣ ለሰው ልጅ ክብርና ምቾት ቅድሚያ የሚሰጥ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ አዲስ የከተማ ልማት ባህል እየተገነባ ነው።
የወንዞቻችን ትንሳኤ የከተማችን ትንሳኤ ነው፤ አዲስ አበባ ከተማነቷን በውበት፣ በአረንጓዴነት፣ በኑሮ ጥራትና በሰው ተኮር ልማት እየቀየረች መሆኑን ከአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡