AMN- ጥቅምት 26/2019 ዓ.ም
የአፍሪካ የወደፊት ብልፅግና በወጣቶች አመራርና ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ ነው ሲሉ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አክሊሉ ታደሰ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሁለተኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ “ለዕድገት መምራት፡ የአፍሪካን የኢኮኖሚ የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚቀርፁ የፖለቲካ ፓርቲዎች” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
በጉባኤው ላይ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አክሊሉ ታደሰ (ዶ/ር)፤የአፍሪካ የወደፊት ብልፅግና፣ ሰላምና ዴሞክራሲያዊ እድገት በወጣቶች ንቁ ተሳትፎና አመራር ላይ እንደሚመሰረት ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ በንግግራቸው፤ ከአፍሪካ ሕዝብ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው ከ25 ዓመት በታች የሆነ ወጣት መሆኑን ጠቅሰው ወጣቶች የልማት ተጠቃሚዎች ብቻ ሳይሆኑ ሥራ ፈጣሪዎች፣ የሰላም ግንበኞችና የለውጥ አራማጆች መሆናቸውን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የወጣቶችን ማብቃት በልማት አጀንዳዋ ማዕከል ላይ በማስቀመጥ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በሥራ ፈጣሪነት፣ በፈጠራና በአመራር ልማት ላይ ኢንቨስት እያደረገች መሆኑንም ጠቁመዋል።
በሀገሪቱ ከ50 በመቶ በላይ የአመራር ቦታዎች በወጣቶች መያዛቸውን በማንሳት ወጣቶች የነገ መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ የዛሬው የለውጥ አራማጆች መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ወጣቶች በፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ እንደ መራጮችና የምርጫ ዘመቻ ተሳታፊዎች ብቻ መታየት እንደሌለባቸውም ገልጸው፤ በፖሊሲ ቀረጻ፣ በውሳኔ አሰጣጥና በሃገር አስተዳደር ውስጥ እኩል አጋሮች ሆነው መሳተፍ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የወጣቶች ሥራ አጥነት፣ ግጭት፣ የአየር ንብረት ለውጥና የቴክኖሎጂ ሽግግር የመሳሰሉ የአህጉሪቱ ተግዳሮቶች ያለ ወጣቶች ንቁ ተሳትፎ ሊፈቱ እንደማይችሉም አመልክተዋል።
የአፍሪካን እድል በተሻለ መሰረት ላይ ለማስቀመጥ የወጣቶችን እዉቀት ጉልበት እና ክህሎት በተግባር መጠቀም ያስፈልጋልም ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ ወጣቶች የነገ ሀገር ተረካቢ ብቻ ሳይሆን የዛሬ ሀገር ገንቢ መሆናቸውን በፅኑ ታምናለች ያሉት ሚኒስትሩ ወጣቱም ለሀገሩ ግንባታ የማይተካ ሚናውን በውል እያረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡
ወጣቶች የስራ ፈጣሪ ተመራማሪ የሀገር ኢኮኖሚ ዘዋሪ የማህበራዊ መስተጋብር የልህቀት ማሳያ የፖለቲካ ዘርፉም ጠበብቶች እየሆኑ ነዉ ያሉት አክሊሉ ታደሰ (ዶ/ር) ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
“የወደፊቱ ዕጣ ፈንታ የወጣቶች ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም የወደፊቱ በወጣቶች ዛሬ እየተገነባ ነው” በማለት፣ ወጣቶችን ማመን፣ ማብቃትና ከእነርሱ ጋር በእኩልነት መሥራት እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
በታምራት ቢሻው እና በተመስገን ይመር